በመዲናዋ ዕጣ የወጣባቸውን 68 ሺህ ቤቶች በሦስት ወራት ለማስረከብ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ዕጣ የወጣባቸውን 68 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለዕድለኞች ለማስረከብ እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በመዲናዋ ዕጣ ወጥቶባቸው ለዕድለኞች ያልተላለፉ 68 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስረከብ እየተከናወነ ስላለው ተግባር ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት 139 ሺህ ቤቶችን በመገንባት ላይ እንደሆነና ቤቶቹ በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ከቤቶቹ ግንባታ በተጨማሪ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች እንዲሟላላቸው ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን በተያዘው ዕቅድ መሰረት ለማጠናቀቅ የስራ ተቋራጮች 24 ሠዓት በመሥራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል አቶ ሽመልስ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ያስሚን ወሀብረቢ በበኩላቸው፥ አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን በሽርክና፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት እያስገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት ከሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ከ12 ሺህ በላይ ዜጎች በማሕበር እንዲደራጁ በማድረግ የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አማራጭ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቤቶቹ ሲገነቡ የገንዘብ ችግር እንዳያጋጥም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ማለታቸውን የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመላክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን