Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር  ዐቢይ የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያደረጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐቢይ አህመድ 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያደረጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አመሰገኑ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቋል ። ጉባኤ የአፍሪካ ኅብረትን ወደ ተሻለ ደረጃ ያደረሰ ሲሆን የአህጉሪቱን ፓለቲካዊ ፣ ኢኮነሚያዊና ማህበራዊ ዕድገትና አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ተወስነውበታል ። በዚህ ጉባኤ ላይ 32 የአፍሪካ ፕሬዝዳንቶች ፣ 3 ምክትል ፕሬዝዳንቶች ፣ 7 ጠቅላይ ሚኒስትሮችና 3 ከአፍሪካ ውጪ የመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሳትጸውበታል ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ጥንካሬ የአልማዝ መሠረት ሆና ኖራለች ። ለአፍሪካውያን ነጻነት ያደረገችው ትግል ሲሳካ ፤ የአፍሪካውያን ሁለንተናዊ አንድኘዠነት እንዲመጣ ጥረት አድርጋለች ፤ በማድረግ ላይም ትገኛለች ። ይህ ትግልና ጥረት የኢትዮጵያ መንግስታት በዘመናት ያልቀያየሩ አቋማቸው ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብም አብሮነት የኖረና የሚኖር እምነቱ ነው ። 33ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤም ያስተናገድነው በዚህ መንፈስ ነው ።

ይህ የመሪዎች ጉባኤ በተሳካና ሀገራችንን በሚያስመሰግን መልኩ ተጠናቋል ። ለዚህ ጉባኤ ስኬት የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በጉባኤው ምክንያት ያጋጠመውን የአንዳንድ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል በጸጋ በመቀበል ፤ ከተለያዩ አካላት ለሚሰጡ መመሪያዎች አስከባሪ በመሆን የዜግነት ግዴታውን ተወጥቷል ። የፖሊስ አካላት ብርቱና ዘመናዊ የቅድሚያ ልምምድ በማድረግ በአስተማማኝ መልኩ የከተማውን ጸጥታ ጠብቀዋል ። የደኅንነት አካላት እጅግ ስልጡን በሆነ መንገድ የተቀላጠፈ የመረጃና የደኅንነት አገልግሎት ሰጥተዋል ። የሪፐብሊካን ዘብ አባላት ለሃያ አራት ሰአታት የእንግዶችን አከባቢዎች ፣ የጉባኤውን አከባቢና የመመላለሻ መንገዶችን ደኅንነት በማስጠበቅ የብረት በር ሆነዋል ። ባለ ሆቴሎችና የሆቴል አገልጋዮች ኢትዮጵያን የሚያስመሰግን መስተንግዶ አቅርበዋል ፤ ዲፕሎማቶችና የፕሮቶኮል ባለሙያዎች ሂደቶቹ በሙሉ ደረጃውን የጠበቀና የተቀላጠፈ እንዲሆን አስችለዋል ። የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች የሠመረ አገልግሎት አበርክተዋል ። ሌሎችም ወገኖች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በመወጣት ኢትዮጵያ የብርቱዎች ሀገር መሆንዋን አስመስክረዋል ። ሁሉም አካላት ላደረጉት አገር የሚያኮራ ተግባር በራሴና በኢትዮጵያ መንግስት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ።

ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ ፤ አቅማችንን ሁሉ አስተባብረን ፤ ህመሞቻችንን ሁሉ ተቋቁመን ከሰራን እንዴት ውጤታማ እንደምንሆን የዚህ ጉባኤ ስኬት ብዙ ነገሮችን ያስተምራል ። አፍሪካውያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በመስተንግዷችንና በተቀላጠፈው አገልግሎታችን ተደስተዋል ። አዲስ አበባ ዋና ከተማ መሆኗን በተግባር እንዲያረጋግጡ አድርገናቸዋል ።

ይህ መልካም ስም ለብዙ አፍሪካዊ ስኬቶች መጠቀም አለብን ። አፍሪካውያን በጋራ ለመስራት ፤ በጋራ ለመማር ፤ በጋራ ለመነገድ ፤ በጋራ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር በጋራ ሀብቶቻችንን ለማልማት ዕድል እንዳለን አይተናል ።

በመደመር ዕሳቤ ጠንካራ ውስጣዊ ዐቅምና አንድነትን ፈጥረን የተሻለች አፍሪካን ወደ ማየት መሸጋገር አለብን ። መጀመሪያ ከእኛ እርስ በእርሳችን ተናበንና ተጋግዘን በመስራት ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አቅም እንፍጠር ። ቀጥሎም ከጎረቤቶቻችን ጋር ቀጠናዊ ትብብርና ትግግዝን እናስፋ ፤ ከዚያም አፍሪካውያን በዓለም ላይ አንድ ሆነን በጋራ የምንቆምበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል እንገነባለን ። ለዚህም በትንሽ በትልቁ ጉልበታችንንና ጊዜያችን መጨረሱን ትተን ማርሽ በሚቀይር ነገር ላይ ዐቅማችንን እንድናውለው ጥሪዬን አቀርባለሁ ።

በድጋሚ ይህ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዲሳካ ሌት ተቀን ለሰራችሁ ሁሉ ምስጋናዬን እያቀረብኩ የሀገራችን የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካም ይሄው ትጋት እንዲቀጥል አደራ እላለሁ ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር !
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የካቲት 03 ቀን 2012 ዓ.ም

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.