Fana: At a Speed of Life!

በብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚከሰተውን የእሳት አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ስልጠና ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ)በብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚከሰተውን የእሳት አደጋ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል የሚያስችል በንድፈ ሀሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና መሰጠት ተጀመረ፡፡
 
ብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚከሰተውን የእሳት አደጋ ቀድሞ ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ውስንነት ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ድርጅት እና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ለ11 ቀናት የሚቆይ ስልጠና ዛሬ በጎንደር ከተማ መስጠት ጀምሯል፡፡
 
ስልጠናው ለብሔራዊ ፓርኮች ከፍተኛ ስጋት የሆነውን የእሳት አደጋ ለመከላከል የሚስችል የአቅም ግንባታ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
 
ስልጠናው አገራዊ ቅርፅ ይዞ እንዲሄድ በርካታ ባለሙያዎችን ያካተተና ሁሉንም የጥበቃ ቦታዎችን ለመታደግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል።
 
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ተወካይ አቶ አብርሀም ማርዬ ÷ስልጠናው ሁሉን ያካተተ መሆኑ አገራዊ የሆነ ቅንጅታዊ አሰራርን ለመፍጠር እና አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
 
በተጨማሪም የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ወርቁ ለምለሙ ÷መሰል ስልጠናዎች የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ፣ ሁሉንም ብሔራዊ ፓርኮችን ከአደጋ ለመከላከል እና የባለቤትነት ስሜትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
 
በስልጠናውም ከሁሉም ብሔራዊ ፓርኮች፣ ከባሌና ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርኮች አዋሳኝ ወረዳዎች፣ ዞኖችና ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.