Fana: At a Speed of Life!

በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ የሞከረው አሸባሪው ህወሃት በተባበረ ክንድ እየተደመሰሰ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 05፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ሕዝቡ ከአገር መከለካያ ሰራዊት ጋር በመሆን በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ የሞከረውን አሸባሪ ቡድን በተባበረ ክንድ እየደመሰሱት መሆኑን የካሳ ጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ገለጹ።
የካሳ ጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ መሓመድ ኑር ሳሊን፤ አሻባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ በአፋር ክልል የኢትዮ ጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት በባቲ በኩል ሚሌን ለመያዝ ወረራ መክፈታቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም አሸባሪዎቹ በአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ሕዝቡ የተባበረ ክንድ እየተደመሰሱ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ መስመር ጠላት ሚሌን ለማያዝ በማሰብና የጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት ላለፉት 13 ቀናት የማጥቃት ሙከራ ቢያደርግም በተቀናጀ መልሶ ማጥቃት ሳይሳካለት እየተመታ መሆኑን ጠቁመዋለ።
በዚህም ጠላት ከባድ ኪሳራ እያስተናገደ ይገኛል ያሉት አቶ መሀመድ የማጥቃትና አካባቢውን የማጥቃት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ምክትል ስብሳቢ መዲና መሓመድ ኢብራሒም፤ የአፋር ክልል የጸጥታ ሃይልና ሕዝቡ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ተቀናጅተው በመመከት ጠላት ድል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
‘ዳጉ’ በሚባለው የአፋር ባህላዊ የመረጃ መለዋወጫ መንገድ የአካባቢው ማህበረሰብ የጠላትን እንቅስቃሴ በመከታተል መረጃ እያደረሱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም የጸጥታ ሃይሎ የጠላትን ዱካ ተከትሎ በማሳደድና በመደምሰስ የጥፋት ምኞቱ እንዳይሳካ እያደረገው መሆኑን ምክትል ስብሳቢዋ ተናግረዋል።
ከአፋር ክልል ልዩ ሃይል ምክትል ኮማንደር እስማኤል አህመድ፤ ሕዝቡ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይንበረከክ በየገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በጀግንነት እየተዋጋ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠላት ብዙ ሰራዊት ያለውና ብዙ የታጠቀ አስመስሎ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን ለማደናገር ቢሞክርም ሊሳካለት አልቻለም ብለዋል።
ይህም በመሆኑ የአፋር ሕዝብ፣ ሚሊሻና ለዩ ሃይል ጠላትን በገባበት ሁሉ እየተከታተለ ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፍ እያደረገው ነው ብለዋል።
በአውደ ውጊያው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የክልሉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የጸጥታ አካላት ጠላት ከገባበት እንዳይወጣ ባለበት እያስቀሩት መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.