Fana: At a Speed of Life!

የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል አማካሪ ካውንስል ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል አማካሪ ካውንስል ተመስርቷል።

የፕላን እና ልማት ኮሚሽን በዛሬው ዕለት በግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ የሚስተዋሉ ችግሮች እና ተግዳሮቶችን መቅረፍ የሚያስችል ገለልተኛ አማካሪ ካውንስል ምስረታ ስነ ስርዓት አካሂዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጽም አሰፋ፥በሀገሪቱ የተጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የ10 ዓመት እቅድም የግሉን ዘርፍ እውነተኛ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ነው የገለጹት።

መንግስት ቀድሞ በነበረው አሰራር አይቀጥልም ያሉት ኮሚሽነሯ፥
በቀጣይ ለግል ባለሀብቱ ድጋፍ የማድረግ፣ የልማት አቅጣጫዎችን የመጠቆም፣ህግን የማስከበርና መሰረተ ልማትን የማሟላት አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

በመድረኩ ኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ሚና ማጎልበት የሚያስችል አማካሪ ካውንስል ተቋቁሟል።

አማካሪ ካውንስሉ ባለሃብቶች፣ የንግድ እና የተለያዩ ዘርፍ ማህበራት አባልት እና ተወካዮች የተካተቱበት 12 አባላት ያሉት መሆኑ ተገልጿል።

በውይይቱ የካውንስሉን አጠቃላይ አሰራር እና ተያያዥ ጉዳዮች ባካተተው መነሻ ሃሳብ ዙሪያ ውይይት ተካሄዷል።

የቀረበው መነሻ ሰነድ ከዳበረ በኋላ የመጨረሻውና በካውንስሉ የፀደቀው ሰነድ መመሪያ በመሆን እንደሚያገለግል ተገልጿል።

ካውንስሉ በየጊዜው እየተገናኘ በዘርፉ በሚስተዋሉ ችግሮች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም እቅዶች እና ፖሊሲዎች ዙሪያ በመምከር የመፍትሄ ሃሳብ እንደሚጠቁም ተመላክቷል።

በፋሲካው ታደሰ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.