Fana: At a Speed of Life!

በጋይንት ጋሸና ግንባር የከተተው ሕዝባዊ ሠራዊት ግዳጁን በብቃት እየፈጸመ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከምዕራብ ጎጃም ዞን ወደ ጋይንት ጋሸና ግንባር የከተተው ሕዝባዊ ሠራዊት የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየፈፀመ መሆኑን አባላቱ ተናገሩ፡፡
 
የሕዝባዊ ሠራዊቱ አባላት ወደ ግንባር ካቀኑበት ዕለት ጀምሮ ስለግንባሩ አጠቃላይ ሁኔታና ስለ ጠላት አሰላለፍ በቂ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል፡፡
 
በዚህ መሠረትም የተሰጣቸውን ግዳጅ በአግባቡ በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡
 
የሕዝባዊ ሠራዊት አባላቱ ጠላትን እስከመጨረሻ ሳያጠፉ ወደቤታቸው ላለመመለስ ሥነልቦናዊ ቁርጠኝነትን ተላብሰዋል፡፡
 
መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ የተፈጠረው ጥምረት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደፈጠርም ተናግረዋል፡፡
 
ሕዝቡ ክብሩን ሊያስጠብቅ የሚችልበትን ግንዛቤ ይዞ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ሕዝባዊ ሠራዊቱን የሚመሩት የደንበጫ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ደጀኑ በላይ ተናግረዋል፡፡
 
የክልሉን እና የሀገሪቱን ክብር በአጭር ጊዜ ወደነበረበት ለመመለስም የዞኑ እና የደንበጫ ከተማ አስተዳደር አሸባሪውን ኀይል ለመደምሰስ ሕዝባዊ ሠራዊት ወደ ግንባር ማዝመታቸውን አስታውቀዋል፡፡
 
ሕዝባዊ ሠራዊቱ እስከመጨረሻ ተፋልሞ የሕዝቡን ሕልውና የማረጋገጥ እና የአባቶቹን ታሪክ የመድገም ወኔ ሰንቋል ያሉት አቶ ደጀኑ÷ ዞኑ በበቂ ደረጃ ስንቅና ትጥቅ እያቀረበ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
 
በግንባሩ ወታደራዊ ልምድ ያላቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለሕዝባዊ ሠራዊቱ ስልጠና እየሰጡ መሆኑን አሚኮ ዘግቧል፡፡
 
ስልጠናውን ከሚሰጡት መካከል ሃምሳ አለቃ ቅባቱ ግርማ እንዳሉት÷ ሕዝባዊ ሠራዊቱ በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት እና ባልደፈር ባይነት ወኔ ነው ወደ ግንባር ያቀኑት፡፡
 
ሕዝባዊ ሠራዊቱ ግንባር ካለው የወገን ጦር ጋር የፈጠሩት ቅንጅት ጠላትን በአጭር ጊዜ ድባቅ ለመምታት እንደሚያግዝ ሃምሳ አለቃ ቅባቱ ተናግረዋል፡፡
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.