Fana: At a Speed of Life!

ትህነግ የዓለማችን አሸባሪዎች የፈጸሙትን ወንጀል አሟልቶ ፈጽሟል- አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ትህነግ በዓለማችን ያሉ አሸባሪዎች ሁሉ የፈጸሙትን ወንጀል አሟልቶ የፈጸመ መሆኑ እየታወቀ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ለቡድኑ ሲወግኑ መታየታቸው አሳዛኝ እንደሆነ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ገለጹ፡፡

አምባሳደሩ በካርቱም ተቀማጭ ለሆኑ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሠጥተዋል፡፡

በወቅቱም አንዳንድ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከዕውነታ የራቀ የፈጠራ መረጃ በማሰራጨት የኢትዮጵያን ገፅታ ጥላሸት እየቀቡ በመሆኑ ሱዳናውያን እና ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ዕውነታውን እንዲረዱ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ በማያያዝም ‘‘የአሸባሪው ቡድን ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ እንደሆነና አዲስ አበባም ከበባ ውስጥ ናት’’ በሚል የፈጠራ መረጃ በማሰራጨት ውዥንብር እየፈጠሩ እንደሆነ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በወሬና በሽብር የሚፈርስ አገርና ህዝብ ስለሌለን ኢትዮጵያ ባጠረ ጊዜ ሠላሟን እንደምታረጋግጥ፣ ለዚህም በየግንባሩ በሠራዊታችን ስለተመዘገቡ ድሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ የተሰጠውን መግለጫ መመልከት ብቻ በቂ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

የሰውን ልጅ ብቻ ሳይሆን እንስሳትን ጭምር የሚገድል ወንጀለኛ መሆኑ እየታወቀ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃንም ሆኑ ሌሎች አካላት ለዚህ ቡድን ሲወግኑ መታየታቸው አሳዛኝ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

በማያያዝም የመረጃ ዕጥረት ላለበት ክፍል ትክክለኛ መረጃ ማድረስ ከመገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅ መሆኑን፤ ነገር ግን ተጨማሪ አጀንዳ በመያዝ የአንድን አገር ሠላምና ደህንነት ለማወክ መተባበር ግን ተቀባይነት የሌለው አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የዕለቱ የገለፃ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት በቅርብ እንደሚከታተሉም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የሱዳንን ሠላምና ልማት ኢትዮጵያውያን እንደራሳቸው ሰላምና ልማት እንደሚያዩት፣ አሁን አገሪቱ የገጠማትን ችግርም ቢሆን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሱዳናውያን በራሳቸው የመፍታት ብቃቱ አላቸው የሚል ጽኑ- ዕምነት በኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ዘንድ እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.