ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊት አባላት እንክብካቤ የሚያደርጉት እናት
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጉዳት ደርሶባቸው በጦር ሃይሎች አጠቃላይ ሆስፒታል ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት በተከታታይ እያሳዩት ያለው ደጀንነት ብቻ ሳይሆን የእናትነት እንክብካቤ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ነው፡፡
ወይዘሮ ሊዲያ አብርሃም ይባላሉ፡፡ ትውልድና ዕድገታቸው በአዲስ አበባ ነው፡፡ ስለዚች የበጎ ምግባርና የሀገር ወዳድ ተምሳሌት፤ የሰራዊታችን ደጀን የሆኑ ኢትዮጵያዊ እናት እንክብካቤ ለመመልከት በጦር ሃይሎች አጠቃላይ ሆስፒታል ተገኝተናል፡፡
ከቆይታ በኋላ ወይዘሮ ሊዲያ ወደሚመጡበትና ለሀገራቸው ሕልውና በጀግንነት ሲፋለሙ ጉዳት የደረሰባቸው የጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን አባላት ወደሚገኙበት ማረፊያ ስናመራ ከመኪና ውስጥ ብዛት ያለው የሀገራችን ባህላዊ መሶቦች ፤ ከሸክላ የተሰሩ የምግብ መያዣዎችና የተለያዩ ምግብ የያዙ ዕቃዎች ቁስለኞቹ ወደ ሚገኙበት ክፍል ይጓጓዛሉ፡፡ እኛም መምጣታቸው ስለገባን ተከታትለን ገባን፡፡
ኢትዮጵያዊ ደም ግባት ፤ ደግነትና ጀግንነት ከፊታቸው የሚነበበው ወ/ሮ ሊዲያ፥ ከሚረዷቸው ሴቶች ጋር በመሆን የመመገቢያ ጠረጴዛ ላይ ያመጧቸውን ምግቦች ደርድረው በቁስለኞች መሃል የቡና ሲኒያቸውን አሰናድተው ተቀመጡ፡፡
ነገሩ ለኛ ነው እንጂ ግራ የገባን በመኖሪያ ቤታቸው እያዘጋጁ ለቁስለኞች የሚጠግኑ ምግቦችንና ፈሳሽ መጠጦችን ሆስፒታል በማምጣትና በመመገብ ቤተኛ መሆናቸውን ቆይተን ተረዳን፡፡
በደቂቃ ውስጥ የሆስፒታሉ ማረፊያ ወደ ትልቅ የምግብ አዳራሽነት ተለወጠ፤ በንፅሕና ታሽገው የመጡት የምግብ ሳህኖች ሲከፈቱ ሽታው አካባቢውን አወደው፡፡
ካቀራረቡት ቡና ላይ በመነሳት ለሁሉም ቁስለኞች ከፈለጉት ምግብ እያጣቀሱ በፍቅርና በርህራሄ ሲያስተናግዱ ከአብዛኛው የሰራዊትና የስታፍ አባላት ዓይን ላይ የደስታ እንባ ይታይ ነበር፡፡
ወ/ሮ ሊዲያ ፣ ምግብ የሚፈልጉትን ከመገቡ ፤ ያልፈለጉትን ደግሞ በወተትና በቅቤ የተሰራውን አጥሚት እንደ እናት እየተዟዟሩ እንዲጠጡ ካደረጉ በኋላ የተወሰኑ ሰዎችን አስከትለው ውጭ ወደ ቆሙት መኪናዎች ተያይዘው ወጡ፡፡
ምን ቀርቶ ይሆን? የሁላችንም ጥያቄ ነበር፡፡
ከአፍታ በኋላ ተከታትለው ሲገቡ በሁሉም እጅ ያማረ ባህላዊ ጣባ ይታያል፡፡ ሴቶቹ ጣባዎቹን እንደያዙ ወደ ሴቶች ክፍል ሲገቡ እኛም ተከታትለን ገባን፡፡
ወ/ሮ ሊዲያ የሴቶቹን ፀጉር እየዳበሱ የያዙትን ጣባ ከፍተው ለአናት ተብሎ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀውን ቅቤ መቀባት ጀመሩ፡፡
ሰራዊቱን ለመጠየቅ በሆስፒታሉ ተገኝተው የነበሩት የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ አመራሮችና ነዋሪዎች የሆስፒታሉ ስታፍ ሰራተኞች በቆሙበት እምባቸው በዓይናቸው አቅርሮ ነበር ፡፡
በጎ አድራጊዋና ሀገር ወዳዷ ወ/ሮ ሊዲያ ቁስለኞችን ቅቤ ከቀቡ በኋላ ባመጡት ንጹህ ላስቲክና ነጭ ሻሽ ሲያስሩላቸው ሳይ ጠጋ ብለን “ግን እንዴት አሰቡት ቅቤ መቀባቱን?” አልናቸው፡፡
“እነዚህ ለሀገር ህልውና ሲዋደቁ የቆሰሉ ወታደሮችን እንደ አራስ እናት ነው የማያቸው፡፡ በባህላችንም ቅቤ መቀባት ጥሩ ስለሆነ ብዬ ነው፡፡ ደግሞም ከበረሃ ቆይተው ስለመጡ ይጠቅማቸዋል” አሉኝና ወደ ወንዶች ክፍል በመግባት ያመጡትን ቅቤ እየዛቁ ከደቂቃ በፊት ጣፋጩን ምግብ በሰራና ባጎረሰ እጃቸው አሁን ደግሞ ፀጉራቸውን እየደባበሱ ቅቤውን ይቀቡና ሻሹን አስረው ሲጨርሱ ቶሎ እንዲያገግሙ የምርቃትና የመልካም ምኞት በመጨመር እንደሚወዷቸው ይነግሯቸዋል፡፡
እኒህ ጀግኖች ለሀገር ህልውና ሲዋደቁ እኔስ ምን ማድረግ እችላለሁ? ብዬ አስብ ነበር፡፡
ከምንም በላይ ያላቸውን ሕይወት ሳይሳሱ ለሀገር እየከፈሉ ለሚገኙት ጀግኖች የመከላከያ ሰራዊታችን እኔ እንደ ልጆቼና እንደ ወንድሜ ነው የማያቸው፡፡ በመጨረሻም እዚህ መንፈሰ ጠንካራ ጀግኖች “ለጋራ ሀገራችን ሁላችንም በቻልነው መጠን በጋራ መቆም አለብን” አሉን፡፡
ሀገሩን ለማስቀጠል ሕይወቱንና አካሉን ለሚገብረው ጀግናው ሰራዊት የኔ ወጪ በጣም ትንሹ ነው፡፡ በዚህ ተግባሬ ግን ባለቤቴና አሜሪካ የሚኖሩት የባለቤቴ አባት ያግዙኛል፡፡ ይህን በጎ ተግባርም እንደሚቀጥሉበት ነው ነግረውናል፡፡
ምንጭ÷ የመከላከያ ሰራዊት
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!