ከሀገር እስከ ደጀን የኢትዮጵያ ሰራዊት ነን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ ከ200 ሺህ በላይ ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ጸጥታ ለሚጠብቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መሰጠት መጀመሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በፌስቡክ ገጻቸው እንዳሰፈሩት÷ ከሀገር እስከ ደጀን የኢትዮጵያ ሰራዊት ነን ብለዋል፡፡
ዛሬ በመዲናዋ ከ32 ሺህ በላይ የሰፈር አደረጃጀቶች የተደራጁ ከ200 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ነው ስልጠናው መሰጠት የጀመረው፡፡
ሰልጣኞቹም÷ የጠላትን ፕሮፓጋንዳ ተረድቶ የሚያከሽፍ ለከተማዋ የሰላም ዘብ መሆናቸውን ነው ከንቲባ የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱብንን ሁሉ÷ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሴራቸውን በማፍረስ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን አደጋ በብቃት መመከት ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህም የከተማችንን ብሎም የኢትዮጵያችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የከተማችን ነዋሪዎች ‹‹እኔም የሰፈሬ ፖሊስና የሰላም ዘብ ነኝ!›› በማለት በእልህና በቁርጠኝነት ተነስተዋል ነው ያሉት፡፡
ስራቸው ውጤታማ እንዲሆንም ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ትብብር እና ድጋፍ እንዲደርጉ ከንቲባዋ አሳስበዋል፡፡