Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ 15 ሚሊየን ለሚሆኑ ማሳዎች የ2ኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የግርብርና ሚኒስቴር 15 ሚሊየን ለሚሆኑ ማሳዎች የ2ኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች መስጠቱን አስታወቀ።

በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የ˝ካልም ፕሮጀክት˝ በኢትዮጵያ የአርሶ አደር 2ኛ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት የሚስችለውን ፕሮግራም ለማስጀመር በባህር ዳር ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ባለ ድርሻ አካላት እና በአማራ ክልል ፕሮጀክቱ የሚሰራባቸው የዞንና የወረዳ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ትዕግስቱ ገብረ መስቀል፥ በሀገሪቱ ውስጥ ካለው 50 ሚሊየን ማሳ ውስጥ የ20 ሚሊየን ማሳ ቅየሳ መለየቱን ተናግረዋል።

የ2ኛ ደርጃ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም በቅየሳ ከተለዩ 20 ሚሊየን ማሳዎች ውስጥ 15 ሚሊየን ለሚሆኑ ማሳዎች የ2ኛደርጃ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

የይዞታ ማርጋገጫ ደብተሩ መሰጠቱም ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር እንዲኖር ከማድረጉ ባለፈ መሬት ለተያዘለት አላማ እንዲውል የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ደብተሩ የህፃናት፣የአቅመ ደካሞችን እና ሴቶችን መሬት በማስከበር ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።

እንዲሁም የፍርድ ቤት ክርክሮችን በመቀነስ እና በመፍታት አርሶ አደሩ በክርክር የሚያጠፋውን ገንዘብ፣ ጉልበት እና ጊዜ በማስቀረት ምርቱን ማሳደግ ላይ እንዲያውል ያደርጋል ተብሏል።

በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ወደ ስራ የሚገባው ካልም ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ትግራይ ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አቶ ትዕግስቱ ጠቁመዋል።

በቀጣይም በቤኒሻንጉል፣ ሶማሌ፣ አፋር ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ተመላክቷል።

ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፥ በዚህም ለ8 ሚሊየን ማሳዎች የ2ኛ ደርጃ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች ያስረክባል ተብሎ ይጠበቃል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.