ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአየር ንብረት ለውጥ አዲሱ የአሜሪካና ቻይና ግንኙነት ማጠናከሪያ ነው – ሺ ጂንፒንግ

By Alemayehu Geremew

November 16, 2021

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የአየር ንብረት ለውጥ አዲሱ የአሜሪካ እና ቻይና የትብብር መስክ መሆኑን ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ከአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን ጋር ባደረጉት በበይነ መረብ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅትም ቻይና እና አሜሪካ በፓሪስ የተደረሰውን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ለመተግበር ተባብረው መስራታቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት በቀጣይ አነስተኛ የካርበን ልቀት መጠንን እና አረንጓዴ ልማትን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመተግበር ግንባር ቀደም ሆነው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመግታት ከቃላት ባለፈ ተግባር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ያደጉ ሀገራትም በጉዳዩ ላይ ኃላፊነት እና ግዴታ እንዳለባቸው አውቀው በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል።