Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን ችግር በውጪ ጣልቃ ገብነት መፍታት አይቻልም – የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደሮች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ችግር በውጪ አገራት ጣልቃ ገብነት ሊፈታ እንደማይችል እና መፍትሄው ከውስጥ መምጣት እንዳለበት የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደሮች አምባሳደር ቲቦር ናዥ እና አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ ተናግረዋል።
አምባሳደሮቹ የዘር መከፋፈል ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር እንደዳረጋት ገልፀው፤ “ኢትዮጵያውያኖች ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድነትና በሰላም መኖር የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው” ብለዋል።
በኢትዮጵያና በጊኒ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በትራምፕ አስተዳደር ረዳት የውጭ ጉዳይ የነበሩት ቲቦር ናዥ እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ላይቤሪያ እና ዛምቢያ አምባሳደር የነበሩት ዶናልድ ቡዝ ኢትዮጵያውያን ለውጪ ሀይል ግፊት የማይንበረከኩ መሆናቸውን ማስተዋላቸውን ጠቁመዋል።
አያይዘውም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚና ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ሁለቱም ዲፕሎማቶች ከአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ካሮል ካስቲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሲተገበር የኖረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር መሰረት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ችግር የተባባሰው የፖለቲካ አመራሮች ከህዝቡ ድጋፍ ለማግኘት ዘርን መጠቀማቸው ነው ያሉት አምባሳደር ቡዝ፥ በኢትዮጵያ የተሞከረው ዘርን መሰረት ያደረገ የፌደራሊዝም ስርዓት የታሰበውን ውጤት አለማምጣት ለዚህ ልዩነት መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳደረገ አስምረውበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አድርገዋቸው የነበሩ የፖለቲካ መሻሻሎች በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ቦታ የሚሰጣቸው ነበሩ ብለዋል አምባሳደር ቲቦር ናዥ።
በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ ላለው ግጭት አዎንታዊና አሉታዊ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ዲፕሎማቶቹ፥ የኢትዮጵያ ችግር ከመሰረቱ እንዲፈታ ኢትዮጵያኖች አንድ ላይ ተቀምጠው ስለወደፊታቸው መነጋገር አለባቸው ነው ያሉት።
ከኢትዮጵያ ውጪ ያለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለኢትዮጵያ መሆን አለበት ብለው የሚያስቡትን አቅጣጫ ከማዘጋጀት ይልቅ፥ ህዝቡ በራሱ ችግሮቹን መፍታት የሚችልበትን መንገድ በማመቻቸት ብቻ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.