የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አውሮፕላኖችን በኬሚካል የማፅዳት ስራ እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አውሮፕላኖችን በኬሚካል የማፅዳት ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል።
አየር መንገዱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሚያደርጋቸው ከፍተኛ ቅድመ ጥንቃቄዎች አንዱ ከቻይና እና ቫይረሱ ከታየባቸው ሀገራት የሚመጡ አውሮፕላኖችን በኬሚካል የማፅዳት ስራ መሆኑንም አስታውቋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚሆኑ የህክምና እቃዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባቱንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዞቹንና የበረራ ሰራተኛዎቹን ዓለም አቀፍ መስፈርትን በተከተለ መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ጥበቃ እና ጥንቃቄ በማድረግ በረራውን ወደ ቻይና እያከናወነ መሆኑን ከዚህ ቀደም መግለጹም ይታወሳል።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በወቅቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፥ የዓለም አቀፉ የዓየር ትራንስፖርት ማህበር እና የዓለም ጤና ደርጅት ባስቀመጡት መስፈርት መሰረት ተጓዦችን እና የበረራ ሰራተኞቹን ከቫይረሱ ለመጠበቅ እየሰራ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ከቻይና ውሃን ከተማ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲገቡ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፥ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የኢሚግሬሽን ልዩ መስኮት መዘጋጀቱና ከሌላው መንገደኛ ጋር ሳይቀላቀሉ የሙቀት ምርመራ እየተደረገላቸውም ይገኛል።