የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የህግ አፈፃፀም የለም – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

By Feven Bishaw

November 18, 2021

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ዜጎችን በተለየ መልኩ ማዕከል ያደረገ የህግ አፈፃፀም የለም ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

አምባሳደሩ በሳምንታዊ መግለጫቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ቅሬታ እያነሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የኬንያ መንግስት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያንፀባረቀውን አቋም ታደንቃለች ነው ያሉት።

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ጉዳይ አፍሪካዊ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አበረታች ነው ያሉት አምባሳደሩ ሁኔታዎችም ያንን ለማድረግ የሚገፋፋ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የአፍሪካን በጎ ገፅታ ለመገንባት እንደማይሰሩና ይልቁንም የረሃብ እና የጦርነት ጉዳዮችን ብቻ አጀንዳ አድርገው መስራት ላይ እንደሚያተኩሩ ነው የገለፁት፡፡

ስለሆነም የተሳሳተውን ትርክት የሚያቃና የሚዲያ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል በመግለጫቸው።

በሌላ በኩል ሱዳን በአሁኑ ወቅት በራሷ የውስጥ ጉዳይ በመጠመዷ በግድቡም ሆነ በድንበር ጉዳይ ለመወያየት የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለችም ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም በጅቡቲ የሚገኘው ወታደራዊ ጄነራል በኢትዮጵያ ዙሪያ ለሚዲያ የሰጡት አስተያየት ፖለቲካዊ ተደርጎ መወሰድ እንደማይችልና የግል አስተሳሰባቸው እንደሆነ ነው ያነሱት።