የአካቢያቸውን ሰላም ለማስከበር ከፀጥታ ሀይሎች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ወቅቱ አቅምን አስተባብሮ በአንድነት መቆም የሚያስፈልግበት በመሆኑን ከፀጥታ አካላት ጋር በመናበብ አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆኑን የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
የሶዶ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ÷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ውጤታማ ለማድረግ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች መካከል መምህር ምትኩ አየለ ÷ ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የአካባቢያችንና የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብርን መስራት ግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፀጥታ አካላት ጋር በመናበብ አካባቢያቸውን ከሰርጎ ገቦች ለመጠበቅ በህብረት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ነው የተናገሩት።
“ንጋት ላይ ጨለማ እንደሚበረታ ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ብርሃን ጎልቶ የሚታይበት ወቅት አሸባሪው ቡድን ተጨማሪ የወንጀል ድርጊት እንዳይፈጽም በጥንቃቄ እየተሰራ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠላት ተኝቶ እንደማያድር ሁሉ እሳቸውም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እንደማይተኙ ነው የገለጹት።
“ሰርቶ መኖር የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው” ያሉት ሌላው የሶዶ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ወይዘሮ ድንቅነሽ መና ናቸው።
ሀገር ሰላም እንድትሆን አካባቢያቸውን በመጠበቅ ዘብ ከመቆም ባለፈ ልጆቻቸው የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል የኢትዮጵያን ህልውና እንደሚያስጠብቁ ገልፀዋል።
የሶዶ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መቶ አለቃ በየነ ባንጋ እንዳሉት ÷ በሶዶ ከተማ የአሸባሪውን ቡድን በማንኛውም መንገድ የሚደግፉና የሚተባበሩ አካላትን ላይ በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው።
እስካሁንም ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።
“በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚከለከሉትን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲሁም አዋጁን ለተላለፉት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከመስጠት ጀምሮ ህግ የማስከበር ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል” ብለዋል።
ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ ቴክኖሎጂን እንዲሁም ያሉትን በጎ አጋጣሚዎች ለመልካም በመጠቀም አካባቢያውንና ሀገሩን እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
“እንደሀገር የገባንበት ፈተና ቀላል ባይሆንም በተባበረ ክንድ በድል እንደምንወጣው ጥርጥር የለኝም” ያሉት መቶ አለቃ በየነ፣ ይሄ ፈታኝ ወቅት በድል እስኪያልፍ ድረስ ህብረተሰቡ ድጋፉንና አንድነቱን በማጠናከር ለሀገር ሰላም ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!