ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ከተባበሩት መንግስታት የዩ ኤን ሀቢታት ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ከተባበሩት መንግስታት የዩ ኤን ሀቢታት ዋና ዳይሬክተር ማይሙና ሙሀመድ ሻሪፍ ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸው ወቅትም በከተሞች እድገትና ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።
በዚህ ወቅትም በኢትዮጵያ ከተሞች ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ 12 አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለዳይሬክተሯ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ከ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ የተወሰዱና የከተሞችን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ የከተሞችን ሽግግር ማፋጠን ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።
ፕሮጀክቶችን ለመተግበር በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀው፥ ዩ ኤን ሀቢታት ፕሮጀክቶቹን በመተግበር ረገድ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት የዩ ኤን ሀቢታት ዋና ዳይሬክተር ማይሙና ሙሀመድ ሻሪፍ በበኩላቸው፥ ሃገራት የከተማን መስፋፋት ለማስተናገድና በአግባቡ ለመምራት ትኩረት መስጠት አለባቸው ብለዋል።
ዩ ኤን ሃቢታት ኢትዮጵያ የቀረፀቻቸውን ፕሮጀክቶች ለመደገፍ ዝግጁ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፥ ኢትዮጵያ በከተሞች ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች እየሰራች መሆኗን በቅርቡ ካደረጉት ጉብኝት መረዳታቸውን አስታውሰዋል።
በአቡዳቢ እየተካሄደ ያለው የዓለም የከተሞች መድረክ የአፍሪካ ሚኒስትሮች በከተማ ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ከከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision