ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል-የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች
አዲስ አበባ፣የካቲት 4፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዴሞክራሲ ተቋማትና ህዝቡ ከወዲሁ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞች ገለጹ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአፍሪካ ሀገራት ጋዜጠኞች ፥መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ የምርጫ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ ብዥታዎችን በማጥራት ዴሞክረሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
በቦትሰዋና የሚታተመው “ሆም ሜድ አፍሪካ” መጽሄት አርታኢ፣ የፖለቲካ ጉዳዮች ጸሃፊ እና በ2019 ግንቦት ወር በደቡብ አፍሪካ በተደረገዉ ምርጫ ላይ የሲቪክ ማህበረሰብ አካል ሆኖ የመሳተፍ እድል ያገኘው ቦትስዋናዊው ሆቦሌስዊ ሴፓፓኔ ÷ የደቡብ አፍሪካ ምርጫ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ሲቪክ ማህበራት ለማህበረሰቡ የምርጫ ትምህርት እና መብቶችን በማሳወቅ ረገድ የነበራቸውንም ንቁ ተሳትፎ አስታውሷል ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ፖሊሲና ስትራቴጅ በግልጽ ለህዝቡ እንዲደርስ በማድረግ እና አላስፈላጊ ብዥታዎች በምርጫው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳርፉ በማስቻል ረገድ መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁሟል።
በርከት ያሉ ደጋፊዎች ያሏቸዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚደረጉ ሰላማዊ ምርጫዎች ተመሳሳይ ሀገራዊ ሃላፊነት አለባቸዉ የሚለው ጸሃፊው፥ፓርቲዎች ለሰላም የድርሻቸውን ድርሻ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አብራርቷል፡፡
ነጻ፣ተዓማኒ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድም ገዢዉ ፓርቲ ያለበትን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ተገልጿል።
በደቡብ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የውጭ ጉዳዮች አርታኢ ሶፊ ማኮይና በበኩሏ ፥ኢትዮጵያ በቀጣይ የምታካሂደው ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ሆኖ የሚፈለገውን ውጤት ያመጣ ዘንድ ሁሉንም ያሳተፉ የትብብር ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ ጠቁማለች፡፡
ቤኒንያዊው አንሴልሜ ቮዶናይሲ የአመራር እና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ባለሙያ ሲሆኑ እርሳቸውም እንደሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው፥ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ የሰላም መስመርን የተከተለ እና ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሁሉም ባለድርሻዎች የቤት ስራዎች እንዳሉባቸው ተቁመዋል ፡፡
ስለሆነም ለጠቅላላ ምርጫው አስፈላጊ የሆኑ ቅድም ዝግጅቶች ከወዲሁ መጀመር ያለባቸው መሆኑን ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል ።
በአወል አበራ