Fana: At a Speed of Life!

ቋሚ ኮሚቴው ከዓለም ንግድ ድርጅት ልዑካን ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከዓለም ንግድ ድርጅት ልዑካን ጋር ተወያየ።

ውይይቱ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል በምትሆንበት ቅድመ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።

የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰባሳቢ አብዱላሂ ሀሙ፥ ፓርላማው በኢትዮጵያ እና በዓለም ንግድ ድርጅት መካከል የተጀመረው ድርድር ሲያልቅ ስምምነቱን መርምሮ ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ምርቶቿን ከማመጣጠን አንጻርም ሆነ በሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ ከድርጅቱ ማግኘት ያለባትን ልምድ በጥያቄ መልክ ማቅረቧም ተገልጿል።

የዓለም ንግድ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የልዑካኑ መሪ አምባሳደር አለን ዎልፍ፥ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል ያሳየችውን መነሳሳት እና ፓርላማው ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።

የአባልነት ጥያቄው በተያዘበት አኳኋን ከቀጠለም እስከተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ ብዙ ጉዳዮች እልባት ሊያገኙ እንደሚችሉ ዕምነታቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ስለምታገኛቸው ጥቅሞች ገለጻ አድርገዋል።

ድርጅቱን ለመቀላቀል የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያስተባብረውን ክፍል የሚመሩት ሜይካ ኦሺካዋ በበኩላቸው፥ ፓርላማው አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎችን ቀድሞ መጨረስ እንደሚገባው አንስተዋል።

ይህ አካሄድ ወደፊት የሚደረሰውን ስምምነት ለማጽደቅ መሠረት እንደሚጥል መናገራቸውንም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.