Fana: At a Speed of Life!

በብሔር ስም እየነገዱ ኢትዮጵያን ማሸበር ፈጽሞ አይቻልም – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

 

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና በብሔር ስም በመነገድ ኢትዮጵያን ማሸበር ፈጽሞ አይቻልም” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአፍሪካ ርዕሰ መዲና እና የዓለም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ በፕሮፓጋንዳ ለማሸበር የሚደረጉ ጥረቶች የሕልውና ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት የነበሩ ናቸው ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት የውስጥና የውጭ ሃይሎች አዲስ አበባ ስለመከበቧ ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ቢቆዩም አዲስ አበባ ዛሬም ያለምንም ኮሽታ ዕለታዊ ክዋኔዋን መቀጠሏን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ የተከበበችው ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር በተጠንቀቅ በቆሙ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ወደ ከተማዋ የሚገቡና የሚወጡ ነገሮችን በሚገባ ማወቅ አስችሏል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ህዝብ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ያለው በመሆኑ ለአገሩ ህልውና አስቀድሞ ተነስቷል ያሉት ከንቲባዋ፥ መረጃ በመስጠት፣ አካባቢውን በመጠበቅ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በተቀናጀ አግባብ በመስራት በኩል ውጤታማ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 6 ቢሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን የጠቆሙት ከንቲባዋ ህዝቡ ተደራጅቶ አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ባይከሰትም አሸባሪ ቡድኑ በስልጣን ላይ እያለ ዛሬን ታሳቢ ያደረገ የክፋት ዕቅድ እንደነበረው ጠቅሰው፥ በከተማዋ ያቀዳቸው የክፋት ዕቅዶችና ማስፈጸሚያ ስልቶቹ ጭምር እየተጋለጡና እየከሸፉ መሆኑን አንስተዋል።

ለአብነትም በሺዎች የሚቆጠሩ በጦር ሜዳ ብቻ የሚያገለግሉ የነፍስ ወከፍ እና የቡድን ጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ለሽብር ተዕልኮ የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መያዙን አንስተዋል።

“አሸባሪው ቡድን አዲስ አበባን ቢመኛትም፤ ተመልሶ ዳግም አይረግጣትም፤ ቅዠት ነው” ብለዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲን ጨምሮ አንዳንድ የዲፕሎማሲ ተቋማት ዜጎቻቸውን እና ባለሀብቶችን ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ቤት ለቤት ሳይቀር እየዞሩ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ከዕውነት ጋር የቆሙ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራትም በኤምባሲዎቻቸው በኩል አዲስ አባበ ሰላም መሆኗን መስክረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ማንነትን መሰረት ያደረገ ማዋከብ እንዳለ በማስመሰል ከዕውነት የራቀ መረጃ የሚያሰራጩ አካለት መኖራቸውን የጠቀሱት ከንቲባዋ አንድም ሰው በብሔሩ ምክንያት አለመያዙን ገልጸዋል።

ፈቃድ ወስደው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎችም ሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች ሀሰተኛ መረጃን ማስተጋባት ከሕግ ተጠያቂነት ባለፈ አገርንና ትውልድን የሚጎዳ በመሆኑ በሃላፊነት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የመሪዎችን ንግግር ከአውድ ውጭ በማዛባት ማቅረብ የሽብር ቡድኖች የተካኑበት ልማዳቸው መሆኑን ጠቅሰው ያልተደረገን ተደረገ በማለትና የሰዎችን ንግግር ሆን ብለው በማዛባት የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.