Fana: At a Speed of Life!

በ94 ሚሊየን ዶላር የሚከናወን የመስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ94 ሚሊየን ዶላር ወይም በ4 ቢሊየን ብር የከርሰ ምድር ውሃ የመስኖ ልማትና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የመስኖ ልማት ኮሚሽን ከኮሪያ ሩራል ኮሙዩኒቲ ኮኦፖሬሽን ከተባለ ድርጅት ጋር ተፈራርሟል።
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዳ በቾ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት 5 ሺህ ሄክታር መሬትን ከከርሰ ምድር በሚገኝ ውሃ በዘመናዊ መንገድ በመስኖ በማልማት ሃያ ሺህ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ÷ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያና የኮርያ መንግሥታት ባካሄዱት የፋይናንስ አቅርቦት ስምምነት መሠረት በ94 ሚሊየን ዶላር ወይም በ4 ቢሊየን ብር የሚገነባ ነው ብለዋል።
ገንዘቡ በሃያ አምስት አመታት የሚመለስና ለስላሳ ብድር/soft lone/ የሚባለው ዓይነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በመጪዎቹ 12 ወራት ዝርዝር የጥናትና ዲዛይን የሚከናወን ሲሆን በቀጣዩ አንድ ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
በግንባታውም 42 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ቀደም ሲል የተቆፈሩ ጉድጓዶችን ደግሞ በድጋሚ የማጎልበት ሥራን ያካትታል ነው የተባለው፡፡
ፕሮጀክቱ ግብርናን የሚያዘምን ፣ በምርቶች ላይ እሴቶችን መጨመር የሚያስችልና በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ኮርያውያን የእውቀት ሽግግርን የሚያስገኝ፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች ሕይወት የሚቀይር፣ በአዲስ አበባም የሚታየውን የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረት የሚቀርፍ፣ደረጃውን የጠበቅ ምርትም ለመዲናይቱ ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ከመስኖ ልማት ጎን ለጎን ለአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ተቋማትና ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን የሚያካትት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኮሪያ ሩራል ኮሙዩኒቲ ኮኦፖሬሽን (ኬ አር ሲ) በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ዶ/ር ዩን ዶንግ ኩን በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱን የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት መገለጫ መሆኑን ገልጸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

በቢሾፍቱና ሞጆ መሐልም በ10 ጉድጓዶች 600 ሄክታር ላይ ተመሳሳይ ፕሮጀክት ለመተግበር ተሞክሮ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱን፤ አርሶ አደሮቹም በአሁኑ ሰዓት ስንዴና አቮካዶ በመስኖ እያመረቱ መሆናቸው በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ  መገለጹን ከውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.