Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የኤችአይቪ የስርጭት ምጣኔ 0.93 ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ያለው የኤችአይቪ የስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 93 ላይ እንደሚገኝና 669 ሺህ 236 ሰዎች ደግሞ ኤችአይቪ በደማቸው እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

ይህ የተባለው በኢትዮጵያ ለ33ኛ ጊዜ “ኤችአይቪን ለመግታት፣ ዓለምአቀፋዊ ትብብር፣ የጋራ ኃላፊነት” በሚል መሪ ቃል ህዳር 22 የሚከበረውን የዓለም ኤድስ ቀን አስመልክቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ ህዳር 22 ኤችአይቪ/ኤድስ በደማቸው የሚገኝ የማህበረሰብ ክፍሎችንና በኤድስ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦችን ለማሰብ የሚደረግ ክብረ በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ተከብሮ የሚውል ሲሆን÷ በቀጣይም በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና በጋምቤላ እንደሚከበር ነው የጠቀሱት፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተመረጡበት ዋነኛ ምክንያት በፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ አብዛኞቹ ሰራተኞች ወጣቶችና ከቤተሰባቸው ተለይተው የሚኖሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ይህ የዕድሜ ክልል በኢትዮጵያ ከፍተኛ የስርጭት ምጣኔ ያለበት የእድሜ ክልል በመሆኑና በሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች ስለ ኤችአይቪ ያላቸው መሰረታዊ ዕውቀት አናሳ መሆን ለኤችአይቪ ይበልጥ ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ተናግረው ይህም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ቀኑን አስቦ ለመዋል ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኤችአይቪ ከአንድ ሴክተር በዘለለ የብዙዎችን ርብርብ እና የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.