Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 3 ወራት በሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን የተሠራው ሥራ መሻሻል አሳይቷል – የሠላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን የተሠሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የሠላም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሠላምና የጸጥታ ተቋማት የጋራ ውይይት ክልሎች በሠላምና ደኅንነት ላይ በዘጠኝ ወራት የሠሩትን ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

የሠላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ÷ ባለፉት ሦስት ወራት በአብዛኛዎቹ ክልሎች መረጋጋት ለማምጣት የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተሠራው ሥራ ግን በተለየ መልኩ ለሌሎችም ትምህርት መሆን የሚችል ነው ብለዋል፡፡

ክልሉ ለበርካቶች ሞትና ሥደት ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን ሲያስተናግ እንደነበረ ገልጸው ባለፉት አራት ወራት በክልሉ ግጭቶችን መቆጣጠር መቻሉ ለሌሎችም ተሞክሮ መሆን የሚችል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የሀረር ክልል በሠላምና ጸጥታ ላይ መሻሻል ካሳዩ አካባቢዎች የሚጠቀሱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በጸጥታ ጉዳይ ክልሎች ተቀናጅተው መሥራታቸውም በሦስት ወራት ጥሩ ውጤት የታየበት ሌላው ጉዳይ መሆኑንም የሠላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ገልፀዋል፡፡

ሠላምና መረጋጋትን ለማምጣት አበረታች ውጤት የታዬ ቢሆንም ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ በመከላከልና የህግ የበላይነትን በማስከበር ሠፊ ችግር መኖሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ችግሮችን ለይቶ የመከላከል ስራ መስራትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተስፋየ ምሬሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.