Fana: At a Speed of Life!

አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ የምርት ብክነትን በመከላከል የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ የሚያስቸሉ አዳዲስ የሰብል መፈልፈያ ማሽኖችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች በማስተዋወቅ የቴክኖሎጂ ሽግግር መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ፥ ተቋማቸው በምርምር ያቀረባቸውን የቴክኖሎጂ አማራጮች ከማስተዋወቅ ባሻገር ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሰብል መፈልፈያ ማሽኖቹ በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙ እና በሰዓት እስከ 40 ኩንታል በቆሎ በመፈልፈል የምርት ብክነትን ከማስቀረት ባሻገር የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል፡፡

ዶክተር ካሳሁን ቴክኖሎጂዎችንም ይበልጥ በማሻሻልና በማዳበር ለአርሶ አደሮች በቡድንና በግል በረጅም ጊዜ ክፍያ ለማቅረብ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

ለአርሶ አደሮች የቀረቡት እነዚህ የበቆሎ መፈልፈያ ቴክኖሎጂዎች ከዚህ በፊት ያጋጥም የነበረውን የምርት ብክነት በማስቀረት ምርታማነትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ያሉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍ ባለሙያ አቶ ማስረሻ በዛብህ ናቸው፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮም እነዚህን እና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአርሶ አደሮች ለማስተዋወቅና ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር እየሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በቴክኖሎጂ ትውውቁ የተገኙት አርሶ አደሮችም ለሰብል ስብሰባ ያወጡት የነበረውን የጉልበትና ጊዜ ብክነት በመቀነስ የቀረቡት ቴክኖሎጂዎች ችግር ፈቺ በመሆናቸው በቡድንና በግላቸው ገዝተው ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከቴክኖሎጂ ሽግግር መርሃ ግብሩ ባሻገር በቡሬ ዙሪያ ወረዳ በህልውና ዘመቻው ግንባር በመሰለፍ ከጠላት ጋር ለተፋለሙ ዘማች ሚሊሻ አባላትና ቤተሰቦች ግምታቸው 50 ሺህ ብር የሚያወጡ የአልባሳት እና ምግብ ድጋፍ መደረጉን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.