Fana: At a Speed of Life!

ወጣቶች አሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ የጀግኖች አባቶችን አኩሪ ታሪክ ሊደግሙ እንደሚገባ ማህበሩ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ወጣቶች አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድንን በመደምሰስ የጀግኖች አባቶችን አኩሪ ታሪክ ሊደግሙ እንደሚገባ የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለህልውናው ዘመቻው ከ100 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት የአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር ዳኝነት አያሌው÷ አባቶች ሀገራቸው በየወቅቱ የሚገጥማትን ጠላት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ ሳይከፋፈሉ እርስ በርሳቸዉ በመዋደድ ሲደመስሱ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁንም ቢሆን ወጣቱ ተመሳሳይ ታሪክ ሊደግም እንደሚገባ ያሳሰቡት ሊቀመንበሩ ኅብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ የህልውና ዘመቻውን ሊቀላቀል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

አሸባሪው ትህነግ አማራ ጠላቴ ነዉ ሒሳብ አወራርዳለሁ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እገባለሁ ብሎ በመነሳት የአማራና የአፋር ክልሎችን በመውረር የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመ፣ እያፈናቀለ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የመንግሥትና የግል ተቋማትን እያወደመ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

አረመኔውን የጥፋት ቡድን ለመደምሰስ ብሎም እስከመጨረሻዉ የሰላምና ጸጥታ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እያደረጉ ያሉትን ትግል የማኅበሩ አባላት በአድናቆት ያዩታል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባል ሻምበል ባሻ የኔው ÷ አሁን ላይ ወራሪው የትህነግ ቡድን በምድር ላይ የማይተገበር ግፍ በሕዝብ ላይ እየፈጸመ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ወጣቱ አንድነቱን ጠብቆ የዚህን አረመኔ ቡድን ሴራ ማክሸፍ እንደሚጠበቅበት ገልጸው÷ ወጣቱ ጠላትን ከመደምሰስ በተጨማሪ ድህነትን አጥብቆ መታገል እንደሚኖርበት አስረድተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን በ17 ወረዳዎች የሚገኙ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት ለህልውና ዘመቻው የሚውል ከ100 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ የተረከቡት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ጥላሁን መሐሪ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ሃላፊው የማኅበራቱ ድጋፍ ኅብረተሰቡ ለህልውናው ዘመቻ ድጋፍ እንዲያደርግ አርዓያ ይሆናል ማለታቸውን የዘገበው አሚኮ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.