Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋና አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ውድ አፍሪካዊ ወንድም እህቶቼ፣

አፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልገን በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ – የአፍሪካዊነትን ጉዳይ እንደ መጀመሪያ አጀንዳዋ እንጂ እንደ ሁለተኛ አድርጋ ወስዳው እንደማታውቅ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። ለአፍሪካ ነጻነት ያላት አቋም አንድም ቀን ቀንሶ አያውቅም። ለፓን አፍሪካዊነት የምትሰጠው ቦታ ሁሌም ጉልህ ነው። ጥንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ናት። በአፍሪካዊነት ላይ አትወላውልም። ይሄን የኢትዮጵያን አቋም ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች እንደተገነዘቡት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን መሪዎችም በሚገባ ተገንዝበው አጋርነታቸውን በሚያሳይ መልኩ የኅብረቱን ጉባኤ በአካል እዚህ ለማከናወን ያሳለፉትን ውሳኔ ኢትዮጵያ ታደንቃለች።

ወንድማዊ አጋርነታችሁን በምንሻበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የኮሮናን መስፋፋትንና ወቅታዊውን የጸጥታ ሁኔታ እንደ ምክንያት በማንሣት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት ተግባራቸው ኢትዮጵያን አሳዝኖ ነበር። በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚደረጉት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤያት መካከል በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የመጀመሪያው ጉባኤ ከሶስት ዓመት በኋላ ዳግም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በመሆን መንግስት ልዩ ልዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ጉባኤው እዚህ መካሄዱ የሚኖረውን ትርጉም የተገነዘቡና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም፣ ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እና የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን እንዲታዩ ያላትን የጸና መርሕ ከፍ ያለ ዋጋ የሰጡ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱን መርጠዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ደስ ተሰኝታለች፤ እንኳን ደስ ያለን።

ውድ የሀገሬ ልጆች፣

በችግራችንም ሆነ በደስታችንም ጊዜ ቀድመው ከጎናችን የሚቆሙት አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደሆኑ ይታወቃል። የምንጋራቸው ማንነቶች፣ የሚያስተሳስሩን ታሪኮች፣ የሚያመሳስሉን የጋራ ችግሮች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ኢትዮጵያ ለእነሱ ሁለተኛ ቤታቸው ናት። ሰው ወደ ቤቱ ሲመጣ እንደ ቤተኛ እንጂ እንደ ባዳ አይስተናገድም። እናም እጃችንንና ልባችንን ከፍተን ልንቀበላቸው፣ ለትዝታ የሚተርፍ ቆይታ እንዲኖራቸው አድርገን ልናስተናግዳቸው፣ በሰላም እንደመጡ በሰላምና በሐሴት አቆይተን ልንሸኛቸው ይገባል።

አሁን ጉባኤውን ለማከናወን የቀረን ሁለት ሳምንት ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገን ጉባኤውን ማሳካት አለብን። የጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ ትርጉሙ ብዙ ነው። ሰላማችንና ደኅነታችንን የምናስመሰክርበት፣ ለአፍሪካ ጉዳዮች ያለንን አቋም በድጋሚ የምናስመሰክርበት፤ የኢትዮጵያን መልካም ሁኔታ ለአፍሪካውያን ወገኖቻችን በተግባር የምናሳይበት፤ ከዚህም አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የምናገኝበት ጉባኤ ነው። እናም ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል።

የጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፣ እንዲሁም የመዝናኛና ቱሪዝም ሥፍራዎች ከእናንተ ብርቱ ዝግጅት ይጠበቃል። የሚመጡትን እኅትና ወንድሞቻችንን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብለን፣ ምቾትና ደኅንነታቸውንና ጠብቀን ማስተናገድ አለብን። በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርና ሕዝብ – ለአካባቢ ጽዳትና ጸጥታ ትኩረት ሰጥተው ከዛሬ ጀምሮ የሚጠበቅባቸው ሁሉ እንዲያደርጉ አደራ እላለሁ።

ታላቁ የነጻነት ታጋይና የይቅርታ አባት የሆኑት የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ስለ ሀገራችን ሲናገሩ “ኢትዮጵያ በምናቤ ውስጥ ሁሌም ልዩ ሥፍራ አላት” ያሰኛቸው፣ ኢትዮጵያ ቅንነት በተሞላ ፊቷ ተቀብላ ስላስተናገደቻቸው እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። ይህንን ሊናገሩ የቻሉት፣ የሀገራችንን ፍቅር ያልተለየው እቅፏን በማግኘታቸው ነው። እናም ማንዴላን ባከበርንበት ልክ አሁንም የኅብረቱ አባላትን አክብረን እንድናስተናግዳቸው፣ በኩራት የምንጠቅሰው ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትን ከነሙሉ ክብሩ ዳግም እንድንገለጥ አደራ እላለሁ።

ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው በሁሉም መስኮች አሸናፊ ከሆነች ነው። ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ለአፍሪካ የገባነውን ቃል ጠብቀንና አጽንተን መቀጠላችን ነው። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ያላት አቋም መቼም ቢሆን አይለወጥም። የገባችውን ቃልም በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ሆና ማክበሯን ትቀጥላለች። ይሄንን አቋሟን ስለተገነዘቡ አፍሪካውያን ወገኖቻችንን በድጋሚ አመሰግናለሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥር 8፣ 2014 ዓ.ም

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.