Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአገራዊ ምክክሩ ህዝቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገራዊ ምክክሩ ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ለማስቻል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አሳሰበ።

ኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቁሞና 11 ኮሚሽነሮች ተሰይመውለት በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ ይገኛል።

በሚፈጠረው የምክክር መድረክ የህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጠይቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት፥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገራዊ ምክክሩ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ብዙ መስራት ይኖርባቸዋል።

የሲቪል ማኅበራቱ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት አስቀድመው ማህበረሰቡን የማንቃት፣ የማስረዳትና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባም ሆነ በቅድመ ዝግጅት ስራዎቹ የአጋር አካላትን ድጋፍ ሲፈልግ በቅርበት ሊያግዙና ሊደግፉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን እቅዶች መነሻ በማድረግ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።

የምክክር ሂደቱ የተሳካና የሀሳብ የበላይነት የሚጎለብትበት እንዲሆን መደማመጥና ነጻ ሀሳብን መስጠት ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version