Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመተከል ዞን የነበረውን አለመረጋጋት በዘላቂነት ለመፍታት እርቀ ሰላም ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን የነበረውን አለመረጋጋት በዘላቂነት ለመፍታት ”ከልብ የመነጨ እርቅ ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ በግልገል በለስ ከተማ በባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርዓት ክዋኔ እርቀ ሰላም ተካሄደ፡፡

በእርቀ ሰላም ፕሮግራሙ ላይ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ወጣቶች፣ በድርጊታቸው የተጸጸቱ የተሃድሶ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ የጉህዴን አባላት፣ የብሄረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ወጣቶች በተሃድሶ ስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ተግባር በመቀየር ከህዝቦች ጋር የነበረውን አብሮነት በማጠናከር ወደ ልማት ለመግባት የተደረገውን እርቀ ሰላም ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በመተከል ዞን ትጥቅ በመፍታት የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ እርቀ ሰላም የፈጸሙ የጉህዴን አባላት ማንዱራ፣ ድባጤ፣ ቡለን፣ ወምበራና ዳንጉር ወረዳዎች ውስጥ የነበሩ ናቸው።
በእርቀ ሰላም ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ÷የጠላትን አጀንዳ ከማስፈጸም በመቆጠብ የሰላምን አስፈላጊነት ለሌሎች ግለሰቦች ግንዛቤ በመስጠት ወደ ሰላም ተመልሰው ይቅርታና ምህረትን በእርቀ ሰላም በመፍታት ወደ ልማት መግባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የይቅርታና ምህረት ፕሮግራሙ የተካሄደው በጉሙዝ ብሄረሰብ ዘንድ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚታወቀው ባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርዓት ክዋኔን መሰረት በማድረግ መሆኑን ከመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version