Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ 34 የአልሸባብ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባና በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲዘጋጁ የነበሩ 34 የአልሸባብ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ የአልሸባብ አባላትን ህቡዕ የጥፋት ሴራና እንቅስቃሴ ከጥንሰሱ ጀምሮ ሲከታተል ቆይቶ ከሶማሌና ከኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በተከናወኑ ኦፕሬሽኖች 34 የሽብር ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል፡፡
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የአልሸባብ የሽብር ቡድን ሃይማኖታዊ ክንውኖች የሚበዙባቸውን ወቅቶች ጠብቆ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ አንደነበር በደኅንነት ተቋሙ በተደረገ ክትትልና ጥናት ተደርሶበት ነበር፡፡
 
በእዚህም በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ከፍተኛ ጥቃት ለመፈጸም በህቡዕ ሲያሴርና ሲዘጋጅ ቢቆይም፤ የሽብር ቡድኑን ሰንሰለት በመከታተል እና መረጃ በማሰባሰብ ጥቃቱ እንዲፈጸም ሲያቀነባብሩ የነበሩ እና ለእኩይ ተልዕኮው የተዘጋጁ 34 የሽብር ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ታቅዶ የነበረው የጥፋት ሴራ ከሽፏል፡፡
 
በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊፈጸም የነበረው የሽብር ተግባር ከጥንሰሱ ጀምሮ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሚስጥራዊ ክትትል ውስጥ የነበረ መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው፤ አሸባሪዎቹ ጥቃት ለመፈፀም ወደ መጨረሻው ደረጃ ሲደርሱ ከሶማሌ ክልል ፀጥታ አካላት ጋር እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተከናወኑ ኦፕሬሽኖች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ጠቁሟል፡፡
 
መሃመድ ጉሃድ ሙርሰል እና ሽኽ መሃመድ ሁሴን ዑስማን የተባሉ በኢትዮጵያ የአልሸባብ ሴል የምልመላና የሎጀስቲክስ ጉዳዮችን የሚያስተባብሩ ተጠርጣሪዎች ለሽብር እቅዱ ውጤታማነት ያግዛሉ የተባሉ ግለሰቦችን የኋላ ታሪክ በጥንቃቄ በማጥናት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ምልመላ ያደረጉ ሲሆን፤ የተመለመሉትን ግለሰቦች በማደራጀትም ቤት ሰራሽ ፈንጂዎችን ማዘጋጀትን ጨምሮ ሌሎች አውዳሚ የሆኑ የሽብር ጥቃቶችን መፈጸም የሚያስችሉ ስልቶችና የሽብር ቡድኑን አስተምህሮ የተመለከቱ ተከታታይ ስልጠናዎች እንዲወስዱ በማድረግ የሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴ መሪ ተዋናይና አቀነባባሪ እንደነበሩ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
 
ተጠርጣሪዎቹ ለሽብር ተግባሩ ከመለመሏቸው ሰዎች መካከል ሚካል አብዱረህማን ኢብራሂም በተባለ ግለሰብ ስም የተለያዩ የባንክ አካውንቶች በመክፈት በአሜሪካ ሚኒሶታ፣ ሶማሌ ላንድ እና ኬኒያ ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ ወኪሎች ከፍተኛ ገንዘብ ገቢ ሲያደርጉ እንደነበር በክትትል ከተገኙት የሰነድ ማስረጃዎችም ታውቋል፡፡
 
የሽብር ቡድኑ ህቡዕ የጥፋት ሴራና እንቅስቃሴ ረጅም ጊዜ በፈጀ ክትትልና ጥናት መታወቁን ያመለከተው መግለጫው፤ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የሴራው አካል የሆኑ ግለሰቦችም ትስስርና አስተዋጽኦ ተለይቶ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ከውጭ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
 
የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መግለጫ እንዳብራራው በአልሸባብ የሽብር ቡድን ተመልምለው ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርጉ ከነበሩት 34 ግለሰቦች አስሩ በአሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅ አርሲ፣ ምዕራብ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ እና በምስራቅ ሃረርጌ ዞኖች በተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ሃያ አራቱ የሽብር ቡድኑ አባላት በሶማሌ ክልል አፍዴር፣ ዶሎ፣ ጎዴ፣ ጅግጅጋና ሸበሌ የተያዙ ሲሆን፤ በኦፕሬሽኖቹ ላይ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ አካላት እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
 
የሽብር ጥቃት ለመፈጸም የተዘጋጁ ክላሽ ጠመንጃዎች፣ የመትረየስ ሰንሰለቶች፣ የሞርታር ቅንቡላ መያዣ ሻንጣዎች፣ጥይቶች እና ሌሎችም የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ሰነዶችና የባንክ ደብተሮች ከተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት መያዙን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
 
አልሸባብ ህዝበ መስሊሙ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውን የታላቁን የሮመዳን ፆም እንዲሁም የትንሳኤ በዓል የሚከበርበትን ወቅት በመምረጥ ኢትዮጵያን በሽብር ጥቃት በመናጥ በዜጎች ላይ የደኅንነት ስጋት ለመፍጠር በማሰብ ቢንቀሳቀስም በፀጥታና ደኅንነት አካላት ጥንቃቄ የተሞላበት ክትትልና ኦፕሬሽን ሴራው መክሸፉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ አመልክቷል፡፡
 
ቡድኑ በኢትዮጵያ ያደረጋቸው መሰል እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚ በመክሸፋቸው ወደፊትም ሽንፈቱን ላለመቀበል ተመሳሳይ ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል በመጠቆምም፤ መላው ህብረተሰብ የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በመረዳት አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ፣ ልጆቹ በሽብር ቡድኑ እንዳይመለመሉ ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርግ እንዲሁም የአሸባሪዎችን ሴራ በማክሸፍ ረገድ የእስካሁኑን ከፍተኛ እንቅስቃሴና የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡
 
ኦፕሬሽኑ የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽዖ ላበረከቱት የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ አካላት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምስጋናውን ማቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
Exit mobile version