Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በምዕራብ ሸዋ ዞን በ33 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የውሃ ፕሮጀክት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም-ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በ33 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የውሃ ፕሮጀክት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
 
በዚህም የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በኑሯቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው ነው የዞኑ ነዋሪዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
 
በተለያዩ አካባቢዎች የውሃ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ረጅም አመታትን ቢያስቆጥሩም እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም እየሰጡ አለመሆኑ ይነገራል ።
 
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት ከሰሞኑ ምልከታ ባደረገባቸው ጊንጪ እና ሌሎች የምዕራብ ሸዋ ዞን አካባቢዎችም የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በስፋት መኖሩን መታዘብ ችሏል ።
 
ለአብነትም ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው እና በ 33 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የውሃ ፕሮጄክት ከ7 ዓመታት በኋላም ተገቢውን ግልጋሎት እየሰጠ አይደለም።
 
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ተጨማሪ 127 ሚሊየን ብር ተመድቦለት ወደ ስራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩ ተመላክቷል፡፡
 
የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጂነር አቦማ ቴሬሳ÷በዘርፉ የሚነሱ ቅሬታዎች ተገቢ እንደሆኑ እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
 
ቢሮው ለረጅም አመታት የተጓተቱ ፕሮጀክቶች በቶሎ ወደ ስራ ለማስገባት የልየታ ጥናት ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል።
 
ዘንድሮ የዲዛይን ክለሳ ለተከናወናላቸው 80 ለሚደረሱ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ እንደሆነም ተጠቁሟል ።
 
 
በአወል አበራ
Exit mobile version