Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ነገ የሚከበረው የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀንን የምንዘክረው ለተጎዱ ወገኖች በተቻለን አቅም በመድረስ ነው – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና ቀይ ጨረቃ የበላይ ጠባቂ የሆኑት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ቀኑን የምንዘክረው በሰብዓዊነት በመሰጠት፣ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በተቻለን አቅም በመድረስ ነው ሲሉ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፥ ነገ የሚከበረውን የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀንን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ፥ “በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ75ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ64ኛ ጊዜ ‘ደግነት-ለሰብዓዊነት’ በሚል መሪ ቃል በነገው ዕለት የሚከበረው የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን ለእኛ ልዩ ትርጉም አለው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና ቀይ ጨረቃ የበላይ ጠባቂ የሆኑት ፕሬዚዳንቷ ፥ ቀኑን የምንዘክረውም በሰብዓዊነት በመሰጠት፣ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በተቻለን አቅም በመድረስ፣ በደግነት ኃያል አቅም ልንታደጋቸው ባደረግነው እና የበለጠ ተጠናክረን ለመሥራት በምናሳየው ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።

ሀገራችን የገጠማት ችግር ሰፊ፣ ውስብስብ እና ፈታኝ እንደሆነ ግልጽ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፥ ግጭቶች፣ ጦርነት፣ ድርቅ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ የመሳሰሉት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ብዙዎችን ለእንግልት አና ስቃይ ዳርጓል፤ የበርካቶችም ሕይወት አልፏል ብለዋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን እና ብዙ ንብረት መውደሙን ፤ በዚህም የተነሣ ሰብዓዊነት በእጅጉ የተፈተነበት ወቅት እንደነበር ጠቁመዋል።

ይህ የሚጠበቅብንን ሥራ ግዙፍነት ያሳየናል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ፥ ዕለቱን የምናስታውሰው በበጎ ፈቃድ መንፈስ በመመራት ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ ክብር እና እንክብካቤ፣ በደግነት፣ በቸርነት፣ እና በፍቅር በመነሣሣት፣ ስቃይ ለማቃለል ሕይወታቸውን ከመስጠት አንሥቶ፣ ሳይበገሩ የሰብዓዊ ደግነትን ጥግ ላሳዩ፣ በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ተገኝተው ሰብዓዊ አበርክቶዎችን በመስጠት ላይ ለሚገኙ በጎፈቃደኞች፣ የሕክምና ሙያተኞች እና ሠራተኞች ያለንን ከፍተኛ አድናቆትና ክብር በመግለፅ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከወገኖችን ጎን በጽናት በመቆም ሁለገብ ሰብዓዊ ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮጵያውን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ እና አጋሮች በራሳቸው እና በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ስም ያላቸውን አድናቆት እና ክብር መግለጻቸውን የዘገበው ኢቢሲ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

Exit mobile version