Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

30 ሚሊየን ሊትር የሚጠጋ የምግብ ዘይት እየተሰራጨ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር ውስጥ የተመረተ ከ29 ሚሊየን 774 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እየተሰራጨ መሆኑን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
መንግስት የምግብ ዘይት አቅርቦትን ለማሻሻል የሀገር ውስጥ አምራቾች ድፍድፍ ፓልም ዘይት ከውጪ አስገብተው በማጣራት ያለቀለት ዘይት እንዲያመርቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ÷ የተመደበላቸውን የውጪ ምንዛሪ በመጠቀም ከ29 ሚሊየን 774 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት እንዳመረቱ እና እየተሰራጨ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሸሙ የምግብ ዘይት ማምረቻ ድርጅት ከ9 ሚሊየን 943 ሺህ ሊትር በላይ፣ አል ኢምፔክ ከ3 ሚሊየን 301 ሺህ 630 ሊትር በላይ፣ ፊቤላ ኢንዱስትሪያል የምግብ ዘይት ማምረቻ ድርጅት 16 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር አምርተዋል ተብሏል፡፡
27 ሚሊየን 142 ሺህ 416 ሊትሩ ለክልልና ለከተማ አስተዳደሮች የተመደበ ሲሆን÷ 2 ሚሊየን 61 ሺህ 920 ሊትሩ ለሀገር መከላከያ እንዲሁም 57 ሺህ 92 ሊትር ደግሞ ለፌደራል ማረሚያ ቤት ተመድቦ እየተሰራጨ መሆኑን ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች የተመደበላቸውን ኮታ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በመመሪያ ቁጥር 002/2011 በተገለጸ የዋጋ ስሌት መሰረት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ እንዲያደርጉ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡
Exit mobile version