Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል የመሬት ካዳስተር ቆጠራ ከ75 በመቶ በላይ መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሲካሄድ የነበረው የመሬት ካዳስተር ቆጠራ ከ75 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የክልሉ መሬት አሥተዳደር ገለጸ።

በቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አወቀ ሲሳይ እንደገለጹት፥ አርሶአደሩ በመሬት ባለቤትነቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ዓለም በወቅቱ በደረሠበት የቴክኖሎጂ ደረጃ በመጠቀም መሬቱ በካዳስተር ሥርዓት እንዲገባና እንዲቆጠር ሲሰራ ቆይቷል።

ቆጠራው ላለፉት አምሥት ዓመታት መከናወኑን የገለጹት ኃላፊው አሁን ላይ አፈጻጻሙ 77 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

ለቴክኖሎጂው ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ባለመገኘቱም ሥራው ረጅም ጊዜ እንደወሰደ አንስተዋል።

ቆጠራው በተከናወነባቸው የክልሉ አካባቢዎች ግማሽ ያህሉ አርሶአደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የሁለተኛ ደረጃ የባለቤትነት ማረጋገጫ በተወሠደባቸው አካባቢዎች ከመሬት ጋር የተያያዙ ክርክሮች መቀነሣቸውንም ነው ኃላፊው ያስረዱት።

የመሬት ምዝገባው ውጤት ወደ ብሔራዊ የመረጃ ቋት መግባቱን የጠቀሡት ኃላፊው ÷ አርሶ አደሮች በባለቤትነት ማረጋገጫ ዋስትና ከባንኮች ብድር እየወሰዱ መሆኑንም አስረድተዋል።

በበላይነህ ዘለዓለም

Exit mobile version