Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መሆኑን የተለያዩ ላኪ ድርጅቶች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በኩል የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኙ መሆኑን ነው ላኪዎች የገለጹት።

የኤ ኤን ኤች ኢንፖርት ኤክስፖርት የኦፕሬሽን ኃላፊ ፍሰሃ ባራኪ÷የተለያዩ የቅባት እህሎችን ወደተለያዩ የዓለም አገራት መላክ ከጀመሩ 5 ዓመታት ማሰቆጠራቸውን ገልጸው፥ ለገበያ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች በኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት አስፈትሸው መላክ ከጀመሩ በኋላ የጥራት ችግር ገጥሟቸው እንደማያውቅ ነው የተናገሩት፡፡

ምርቶቻቸውን ቀደም ሲል ወደ ቻይናና ቱርክ ይልኩ እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ላይ ወደ ህንድና አረብ ሀገራት ጭምር በመላክ ምርቱ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን አስረድተዋል።

የበላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ ድርጅት የውጪ ንግድ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ምስጋና እሸቴ እንዲሁ÷ በሦስት አገሮች ብቻ የጀመሩት የውጭ ገበያ አድማሱን አስፍቶ ወደ 10 ሀገራት ማደጉን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፍተሻ ማድረጋቸው ደግሞ የውጭ ገበያ መዳረሻቸውን ማስፋቱን ጠቁመው፥  ሌሎች ላኪዎችም ተመሳሳይ አሰራር እንዲከተሉ መክረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቤል አንበርብር÷ ምርቶቻቸውን አስፈትሸው የሚልኩ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በቂ አለመሆኑን እንደተናገሩ የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የተሰማሩ ላኪ ድርጅቶች የሚሰጠውን ምዘና በማለፍ ሁሉም ላኪዎች ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የእውቅና ማረጋገጫ አገልግሎቶች የሚሰጥ ተቋም ነው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version