Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የደቡብ ሱዳን የታጠቁ ሃይሎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፈፀሙት ወረራ የለም – የክልሉ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ሱዳን የታጠቁ ሃይሎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፈፀሙት ወረራ አለመኖሩን የክልሉ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ÷የሪፖርተር ጋዜጣ በሰኔ 19 ቀን 2014 እትሙ የደቡብ ሱዳን የታጠቁ ሃይሎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ወረራ ፈፅሟል ብሎ ያወጣው ዘገባ ስህተት ነው፡፡

አቶ አንድነት የደቡብ ሱዳን የታጠቁ ሃይሎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፈፀሙት ወረራ አለመኖሩን ነው የተናገሩት፡፡

ክልሉ እንደወትሮው በሁሉም አቅጣጫ ሰላም እንደሆነ የገለጹት ሃላፊው÷ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ሱርማ ወረዳ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያዋስን አካባቢ በመሆኑና በሁለቱም አከባቢዎች ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች አርብቶ አደር ስለሆኑ በግጦሽ ሳርና በውሃ ምክንያት አልፎ አልፎ ግጭትና ዝርፍያ ይፈፀማሉ ብለዋል።

አሁንም በአከባቢው የተስተዋለው በአርብ አደሮች የአኗኗር ባህሪይ የተከሰተ ግጭትና አለመግባባት መሆኑን ጠቁመው÷ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እንደ ክልል ከመደራጀት በፊትም የነበረ እንደሆነ አቶ አንድነት አብራርተዋል።

አቶ አንድነት አሁን የአገርቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማሳበብ የሪፖርተር ጋዜጣ በሰኔ 19/2014 እትም ያወጣው ዘገባ ከነባራዊ ሁኔታና ከአውድ ያፈነገጠ እንደሆነና መታረም እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

በድንበር አካባቢ የሚፈጠረውን ግጭትና አለመግባባትን የፌዴራልና የክልል መንግስት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር በውይይት ለመፍታት እንደ ከዚህ በፊቱ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም አቶ አንድነት ተናግረዋል።

የህዝቡን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ የክልሉ መንግስት ቀዳሚ ተግባር ስለሆነ የክልሉን ህዝብና የፀጥታ ሃይሉን በማስተባበር በትኩረት እየሰራ እንደሆነ መጠቆሙንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች በአንፃራዊነት የተረጋጋ ሰላም እንዳለ የገለፁት አቶ አንድነት አሸናፊ ሰላም ለሁሉም ስለሚተርፍ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአከባቢውን ሰላም እንዲያስጠብቅና ለፅንፈኛ ሀይሎች አጀንዳ ጆሮ መስጠት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡

Exit mobile version