Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ53 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በከሚሴ ከተማ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ ከተማ በ53 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተመረቁ፡፡
የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የእዚህ ፕሮጀክት አስገራሚ ገጽታ ሳናገግም በጦርነት ማግስት የአመራር ለውጥ ባደረግንበት ሁኔታ አመራሩ ከሕዝቡ ጋር ቅንጅት ፈጥሮ በመሥራቱ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
ከሚሴ የኢትዮጵያ የአብሮነት ምሳሌት ናት፤ በዚህም የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የጀመርነውን የሰላም እንቅስቃሴ ወደ አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ ይገባናል ብለዋል፡፡
የከሚሴ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ከድጃ አሊ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የልማት ስራዎችን ሰርተን በማስመረቃችን ይህ ቀን ከፍተኛ የድል ቀናችን ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከአካባቢው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ÷ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ውድመቱን ለማካካስ አመራሩ በልዩ ትኩረት ተቀናጅቶ በመሥራቱ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቶችን ለመፈጸምም በ53 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ 16 የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል ማለታቸውን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ በከተማ ተቋማት እና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (UIIDP) መሸፈኑን ጠቁመው÷ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ አና የተዘረፉ የቢሮ ቁሳቁሶችም ለተቋማት መከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version