Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና ዚምባብዌ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ዚምባብዌ በትራንስፖርት እና በመሠረተ ልማት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ተስማምተዋል፡፡

በዚምባብዌ የኢትዮጵያ አምባሳደር ራሺድ ሞሐመድ ከዚምባቡዌው የትራንስፖርት እና የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ፀሐፊ ቴዎዲየስ ቺንያንጋ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይታቸውም የሀገራቱን የትራንስፖርትና የመሠረተ ልማት ዘርፍ ትሥሥር እና ትብብር የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የሁለት ጊዜ የቀረጥ ሥርዓቱን በምክክር ዕልባት ለመሥጠትና የሀገራቱን የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር ብሎም ልማታቸውን ለማፋጠን መምከራቸውም ተጠቁሟል፡፡

አምባሳደር ራሺድ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ስለተደረሰው የሠላም ስምምነት ለቴዎዲየስ ቺንያንጋ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የሠላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ሠላምን ያስቀደመና ግጭት የሚያበቃበትን አማራጭ ያስቀመጠ እንዲሁም አዲስ የሠላም እና የመረጋጋት ዘመንን ያበሰረ ነው ብለዋል፡፡

ቴዎዲየስ ቺንያንጋ በበኩላቸው÷ ከሠላም ንግግሩ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ሥምምነት ላይ በመድረሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው÷ በቀጣይም ዚምባብዌ ለኢትዮጵያ ሠላም የሚጠቅሙ ጥረቶችን ሁሉ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
Exit mobile version