Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተፈጠረውን ሰላም እንደ ትምህርት ያሉ ስብራቶቻችን ላይ ተግተን ለመስራት እድል የሚሰጥ ነው – ፕሮፌሰር  ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተፈጠረውን ሰላም እንደ ትምህርት ያሉ ስብራቶቻችን ላይ ተግተን ለመስራት እድል የሚሰጥ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር  ብርሃኑ ነጋ  ገለጹ፡፡

31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በሀዋሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባዔው “ጠንካራ የትምህርትና ምዘና ስርዓት ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

በመድረኩ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች እና ምሁራን ተገኝተዋል፡፡

ፕሮፌሰር  ብርሃኑ  ጉባኤው በጦርነቱ ምክነንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባትና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመለስ የሚሰራበት ጊዜ ላይ በመካሄዱ ጠንካራ ውይይት ያስፈልገናል ብለዋል።

የ12ኛ ክፍል ፈተናን በአብነት ያነሱት ሚኒስትሩ÷ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ዘርፉ ባለደርሻ አካላትም  ትጋታችውን  እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጉባኤው የሴክተሩ የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸም የሚገመገም ሲሆን÷የ2015 የሥራ እንቅስቃሴ ሚኖረውን አካሄድ በተመለከተም ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በሀብታሙ ተ/ስላሴ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version