Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፖሊስና ህዝቡን ትብብርና በጋራ መስራት የሚያጠናክር ገለልተኛ አማካሪ ቡድን ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖሊስና ህዝቡን ትብብርና በጋራ መስራት የሚያጠናክር ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድን በይፋ ተመሰረተ።

ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ከመንግስት አካላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ያሉበት ሲሆን÷የፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማሳለጥ የሚሰራ መሆኑ ተገልጿል።

አማካሪ ቡድኑ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከሲቪል ማህበራትና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላትን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል፡፡

አማካሪ ቡድኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል በሰብሳቢነት የሚመሩት ሲሆን÷ በፖሊስና ህብረተሰቡ ዘንድ ትብብርና አብሮነትን ማጠናከር እንዲሁም የፖሊስ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ በይፋ መመስረቱን በዛሬው ዕለት አብስረዋል።

አደረጃጀቱ ወንጀልንና የወንጀል ስጋቶችን በመቀነስ ሒደት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይ የወንጀል ስጋትን ለመቀነስና ቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም በማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፖሊስ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ መረጃዎች፣ አቅጣጫዎችና መፍትሔዎችን በጋራ ማስቀመጥና ሌሎችንም ዓላማ መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በክልሎች ደረጃ ተቋቁሞ ውጤት ማስገኘቱ ተገልጿል።

Exit mobile version