Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ብሉልታ ገለጹ፡፡

የኦሮሚያ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት ኦሮሚያ ታምርት ” በሚል መሪ ሀሳብ አምራች ኢንዱስትሪውንና የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ከክልሉ ባለሀብቶች ጋር የንቅናቄ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ ይህ ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በዘርፉ አበረታች ውጤቶች መታየታቸውንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

ወደ 200 የሚደርሱ ማምረት አቁመው የቆዩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉንም ገልጸዋል።

የአምራች አንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ እና የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ ባሳለፍነው አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ መጀመሩን አስታውሰዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ ሆነው የማምረት አቅምን ለማሳደግ በፋይናንስ፣ በመሰረተ ልማት ማሟላት፣ በገበያ ትስስር ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆንና የስራ እድል መፍጠር እንዲችል በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው ÷ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት እና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ፣ ነባሮቹን በማጠናከር ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመድረኩ የፌደራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ እና ሙሉ ዋቅሹሜ

Exit mobile version