Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ ክልል ከ7 ሚሊየን በላይ የመማሪያ መጽሐፍት ታትመው ለተማሪዎች እየተሰራጩ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል 7 ሚሊየን 35 ሺህ በላይ አዳዲስ የመማሪያ መጽሐፍት ታትመው ለተማሪዎች እየተሰራጩ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
 
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ግርማ ባይሳ እንደገለጹት ÷ በኦሮሚያ ክልል ለተዘጋጀው የቅድመ መደበኛ እና ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል አዲስ ስርዓተ ትምህርት የመማሪያ መጽሐፍት በፍጥነት አሳትሞ ለተማሪዎች ለማሰራጨት በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
 
በዚህ መሰረት የመምህራን መምሪያ መጽሐፍትን በቅድሚያ በማሳተም ለሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲሰራጩ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡
 
አዲሱ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ እስከሚታተም ድረስም በቅጂ መልኩ እና በተንቀሳቃሽ ምስል ለተማሪዎች እና መምህራን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
 
አሁን ላይም ከ7 ሚሊየን 35 ሺህ በላይ የመማሪያ መጽሐፍት መታተማቸውን አቶ ግርማ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
ከታተሙት መጽሐፍት ውስጥም 5 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መሰራጨታቸውን አስረድተዋል፡፡
 
በቀጣይም የመማሪያ መጽሐፍቱን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version