Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድነት ለአገራዊ አንድነት መጠናከር እጅግ አሰፈላጊ መሆኑን በማመን ባለፉት የለውጥ አመታት መንግስት ህገመንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀ አኳኃን ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

መንግስት በእምነት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች በዋናነት መፍትሄ የሚያገኙት በራሳቸው በተቋማቱ የውስጥ አሰራር መሆኑን ያምናል።

በመሆኑም በሀይማኖት ተቋማት መንግስት ከህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ውጭ የሆነ መፍትሔ መስጠት እንደማይችል ልንገነዘብ ይገባል።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበና በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ የፓለቲካ ኃይሎች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማዳከም ርብርብ እያደረጉ ነው።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄዱና የሀገርና የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅሳቃሴዎች የክልሉ መንግስት አጥብቆ ይቃወማል።

ለአገራችን ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ዝግጅት እየተጠናቀቀ በሚገኝበት ወቅት ስልጣን በተሰጠው አካል ያልተፈቀደና የደኅንነት ስጋት የሚፈጥር የሕገወጥ ሰልፍ ቅስቀሳ ማድረግ ተገቢነት የለውም።

የክልሉ መንግስት ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ ማናቸውም ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣል።

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይልን ውሳኔ የመፈፀምና የማስፈፀም ህገ-መንግስታዊ ኃላፊነታችንን የምንወጣ መሆኑን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን።

መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃለፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅሳቃሴ ሁሉ ሕዝብ አሰፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደረደርግ ጥሪ እናቀርባለን ፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መንግስት።

የካቲት 3/2015

Exit mobile version