Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ከ223 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል አማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ223 ሺህ ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለፀ፡፡

የአማሮ ልዩ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ፍፁም አራጋው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ÷ በአማሮ ልዩ ወረዳ ለረጅም ጊዜ ዝናብ ባለመጣሉ በልዩ ወረዳው 22 ቀበሌዎች ድርቅ ተከስቷል፡፡

በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በልዩ ወረዳው ከ140 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ  ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው፥ ከ3 ሺህ 500 በላይ የቤት እንስሳትም በድርቁ ምክንያት መሞታቸውን ገልፀዋል፡፡

በልዩ ወረዳው የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች የህብረተሰቡን ተጋላጭነት እንዳባባሱትም ነው ሃላፊው የሚናገሩት።

በድርቁ እና ለረጅም ጊዜ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ በርካት ሰዎች ለአደጋ መጋለጣቸውንም አስረድተዋል፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በተለያየ ጊዜ እርዳታ ቢያደርግም በልዩ ወረዳው ከከተከሰተው ጉዳት አንፃር ድጋፉ በቂ አለመሆኑንም አንስተዋል፡፡

የቡርጂ ሶያማ ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ ጩሎ ጫንዶ በበኩላቸው፥ በቡርጂ ልየ ወረዳ በተከሰተው ድርቅ 83 ሺህ 528 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የገለጹት።

ከዚህ ባለፈም ከ30 ሺህ በላይ እንስሳት መሞታቸውንም ጠቁመዋል።

በዚህም ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለረሀብ፣ ለበሽታ እና ለሞት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡

ከክልሉ መንግስት በተጫማሪ የአካባቢው ተወላጆች እና ግለሰቦች እርዳታ ቢያደርጉም በልዩ ወረዳው ከተከሰተው ድርቅ አንፃር የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት በቂ አለመሆኑን አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም በድርቅ የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት እና መልሶ ለማቋቋም ረጂ ድርጅቶችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረታቸውን ወደ ልዩ ወረዳው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

 

በሚኪያስ አዬለ

Exit mobile version