Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኤክስፖርት ቡና የጫነ ተሽከርካሪን በማገት ቡናውን ወስደዋል በተባሉ 11 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ15 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኤክስፖርት ቡና የጫነ ተሽከርካሪን መንገድ በመዝጋት አስፈራርተው ቡናውን ወስደዋል በተባሉ 11 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቷል።

የኤክስፖርት ቡና የጫነ ተሽከርካሪን በማገትና በማራገፍ ግማሹን ቡና በመሸጥ ለግል ጥቅም አውለዋል የተባሉ ተከሳሾች ናቸው ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው።

ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ የመከላከያ አባል ነው የተባለው ሻንበል ዜና ማርቆስ አለሙ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አባል የሆነው ትንሳኤ ታከለ እና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አባል የሆነው ታምራት ጌታቸውን ጨምሮ አጠቃላይ 11 ግለሰቦች ናቸው ፡፡

ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል ከ7ኛ እስከ 11 ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች በግል ስራ ላይ የሚተዳደሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በተለያዩ ቀናት ኤክስፖርት የሚደረግ ቡና ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ በስልክ በመደዋወል መረጃ በመለዋወጥና በመነጋገር ተሽከርካሪውን አስቁመው ለመውሰድ በመስማማት ዝግጅት ማድረጋቸው በክሱ ተመላክቷል።

በዚህ መልኩ ዝግጅት ካደረጉ በኋላ ከሲዳማ ክልል ዳዬ ቦንሳ ዳዬ ከተማ እና ዳሌ ወረዳ ማንቼ ቀበሌ መነሻቸውን ያደረጉ ኤክስፖርት ቡና የጫኑ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎችን ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በመኪና በመከተል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 አካባቢ ተሽከርካሪዎቹ ላይ መንገድ በመዝጋት እና በማስቆም ሾፌሮችንና ረዳቶችን ማስወረዳቸው ተጠቁሟል፡፡

ሾፌሮችንና ረዳቶችን በማስፈራራት እና በቁጥጥር ስር እንደዋሉ በመግለጽም ቡናውን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን በሌላ አሽከርካሪ በመውሰድ 10ኛ ተከሳሽ በተከራየበት መጋዘን ውስጥ ቡናውን አራግፈው መኪናውን ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሩፋኤል አካባቢ አቁመው መሄዳቸው ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ከ338 ኩንታል በላይ ከታጠበ ቡና ውስጥ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተደረገ ብርበራ 135 ኬሻ የታጠበና የተበጠረ ቡና እንዲሁም ሌላ 33 ነጥብ 5 ኬሻ ደግሞ የታጠበ ቡና በ10ኛ ተከሳሽ መጋዘን ውስጥ ተደብቆ የተገኘ ሲሆን ÷ቀሪው ቡና ግን ተሽጦ ለግል ጥቅም መዋሉ በክሱ ተመላክቷል።

እንደ አጠቃላይ የተከሳሾችን ተሳትፎ በዝርዝር ጠቅሶ ሶስት ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ ክሱ የደረሳቸው ሲሆን ÷ፍርድ ቤቱ ከጠበቃ ጋር ተማክረው ክሱን በንባብ ለማሰማት ለግንቦት 10 ቀን 2015ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

Exit mobile version