Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ፈቃዱ ተሰማ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ላይ በደረሰው የትራፊክ አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

Burning candles on black background, shot with shallow depth of field

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ላይ በደረሰው የትራፊክ አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት ወደ ሻሸመኔ ካምፓስ ለማስተማር ሲጓዙ የነበሩ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሰራተኞች ላይ በደረሰ የመኪና አደጋ ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡

አቶ ፈቃዱ ባስተላለፉት የሃዘን መግለጫ ÷ በዘመናት ውስጥ መምህራን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር እጅግ ፈታኝ እና እልህ አስጨራሽ የህይወት ፈተና በመጋፈጥ ሕዝብ እና ሀገር የጣለባቸውን አደራ ከግብ ለማድረስ በብዙ ይፈተናሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም መምህራን ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ሲከፍሉ እንመለከታለን ነው ያሉት ፡፡

“የአሁን መምህራን የወደፊት ተመራማሪ፣ ሀገር ተረካቢ፣ ትውልድ ፈጣሪ እና በብዙ መልኩ ሀገራችን የምትጠብቃቸውን ጠንካራ ወጣት መምህራንን በትራፊክ አደጋ ማጣታችን እጅግ ልብ ሰባሪ ክስተት ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

“መምህራን ከማይነጥፈው የዕውቀት ማዕዳቸው በሁላችን ህሊና የምንስላትን የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሚከፍሉትን ዋጋ ማድነቅ ግድ ይላል” ብለዋል፡፡

“መምህራን እውን ለማድረግ የምንታገልለትን የብልፅግና ከፍታ ከዳር ለማድረስ እንደ ሻማ እየቀለጡ፤ በመቅለጣቸው ውስጥ ለሚሊዮኖች እያበሩ ሩጫችንን የሚያፋጥኑ የሀገር ባለውለታዎች ናቸው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የትራፊክ አደጋ አስከፊነቱ አደጋው የሚፈጥረው ኪሳራ እና ጥቁር ጠባሳ አለመሻሩ ነው ያሉት ሃላፊው÷ ትናንት በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ያለፉ መምህራን መስዋዕትነት በታሪክ ውስጥ በደማቅ ቀለም ሲወሳ ይኖራል ብለዋል።

Exit mobile version