አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ ማንቼስተር ዩናይትድ ካሜሩናዊውን ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና ለማስፈረም ሥምምነት ላይ መድረሱ ተሰማ።
ክለቡ ለግብ ጠባቂው 47 ነጥብ 2 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ገንዘብ ለመክፈል ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ጋር ሥምምነት ላይ ደርሷል ነው የተባለው።
በቅድሚያ 43 ነጥብ 8 ሚሊየን ፓውንድ እንዲሁም ቀሪውን 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ፓውንድ ክፍያ ደግሞ በተጫዋቹ ብቃት እና ስኬት ላይ ተመስርቶ ለመክፈል መስማማቱን ስካይ ስፖርት እና ቢቢሲ አስነብብዋል።
ግብ ጠባቂውም የላንክሻየሩ ክለብ በአሜሪካ የሚያደርገውን የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ላይ ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።
የ27 አመቱ ግብ ጠበቂ ከዚህ ቀደም ከአሁኑ የማንቼስተር ዩናይትድ አለቃ ቴን ሃግ ጋር በኔዘርላንድሱ አያክስ አምስተርዳም አብሮ መስራቱ ይታወሳል።
በአያክስ የነበረውን ቆይታ በማጠናቀቅም ባለፈው የውድድር አመት የጣሊያኑን ኢንተር ሚላን በመቀላቀል በዘንድሮው ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ችሏል።
ማንቼስተር ዩናይትዱ ከክለቡ ጋር 12 የውድድር አመታት ያሳለፈውን ዴቪድ ዴ ሂያ ኮንትራት የማደስ ፍላጎት ሳያሳይ ከግብ ጠባቂው ጋር መለያየቱ ይታወቃል።
ለዚህ ደግሞ የክለቡ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ‘ለምከተለው የእግር ኳስ አጨዋወት ከእርሱ ይልቅ ኳስን ከራሱ ጎል በጨዋታ የሚያስጀምረው ኦናናን ተመራጭ’ ማድረጋቸው እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።
ኦናና ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ለአምስት አመታት የሚቆይ የኮንትራት ውል እንደሚፈራረም ይጠበቃል።
ክለቡ ከእርሱ ቀደም ብሎ ሜሰን ማውንትን ከቼልሲ ሲያዘዋውር፥ በተጠናቀቀው አመት የክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የነበረውን ማርከስ ራሽፎርድን ደመወዙን ጨምሮ አምስት ተጨማሪ አመታት ለማስፈረም መስማማቱም የሚታወስ ነው።
በሌላ የዝውውር ዜና የብራይተኑን አማካይ ሞሰስ ካይሴዶን ለማዘዋወር 70 ሚሊየን ፓውንድ ያቀረበው የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ጥያቄው ውድቅ ተደርጎበታል።
ብራይተን ለአማካዩ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን የዌስትሃም ዩናይትዱ ዴክላን ራይስ አርሰናልን ከተቀላቀለበት የገንዘብ መጠን ጋር እኩል መሆን አለበት ይህ ካልሆነ ግን ዝውውሩ አይታሰብም ብሏል።