አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃንጋሪ ቡዳፔስት እየተካሄደ ባለው 19ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለፉት ሁለት ቀናት በተደረጉ ውድድሮች ኢትዮጵያ በ4 ሜዳሊያዎች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች አሜሪካ በ3 ወርቅ፣ 2 ነሃስ እና በአንድ ብር ቀዳሚውን ደረጃ ስትይዝ ስፔን በሁለት የወርቅ ሜዳሊያ 2ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
በሁለቱ ቀናት ውድድር ኢትዮጵያ 1 ወርቅ ፣1 ነሃስ እና 2 ብር በአጠቃላይ በአራት ሜዳሊያዎች ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ከዓለም ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች፡፡
በሻምፒዮናው 3ኛ ቀን ዛሬ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ውድድሮች አይካሄዱም።
በነገው እለት በጠዋት ክፍለ ጊዜ በሚደረገው የ1 ሺህ 500 ሜትር እና 5 ሺህ ሜትር የሴቶች ማጣሪያ እንዲሁም ምሽት ላይ በሚደረገው የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ እና በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች ፍፃሜ ኢትዮጵያ የምትሳተፍ ይሆናል፡፡
እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች 18 ሀገራት ሜዳሊያ ሲያገኙ 7 ሀገራት ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ መቻላቸውን ከአለም አትሌቲክስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡