Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሜሪካ ከ3 የፓስፊክ ሀገራት ጋር በጸጥታና ደህንነት ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማማች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የቻይናን ተጽዕኖ ለመቋቋም በማለም ከሶስት የፓስፊክ ሀገራት ጋር ከጸጥታና ደህንነት ጋር በተያያዘ በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጓ ተነግሯል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ከፓላው፣ ከማርሻል ደሴቶች እና ከማይክሮኔዥያ መሪዎች ጋር በቀጣናው ጸጥታ፣ ደህንነትና ኢኮኖሚ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ስምምነቱን አስመልክቶ እንዳሉት÷ አሜሪካ ከፓስፊክ አጋሮቿ ጋር በጋራ በመሆን በሚቀጥሉት 20 ዓመታት በትብብር ትሰራለች፡፡

ለዚህም ዋሽንግተን ለሀገራቱ 7 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ የተስማማች ሲሆን የድጋፍ ስምምነቱ ለሀገራቱ የደህንነትና የገንዘብ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በምላሹ ዋሽንግተን በማዕከላዊ ፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የሚያስችላት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላታል ነው ያሉት፡፡

የፓስፊክ ሀገራቱ መሪዎች በበኩላቸው÷ የተደረገው ስምምነት የሀገራቱን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ታላቅ እርምጃ እንደሆነ መግለጻቸውን ቲአርቲ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version