Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ በመሙላቱ 32 ሺህ ሰዎች ተፈናቀሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በተለያዩ ወረዳዎች 32 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸዉን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋሰትና ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ገለፀ ።

በአፋር ክልል ክረምቱን ተከትሎ እየጣለ ባለው ዝናብ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በ6 ወረዳዎች 32 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን በፅህፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን ገልፀዋል ።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በክልሉ በአዋሽ ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ 7 ወረዳዎች ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት ተጋላጭ ናቸው ።

ይህን ችግር ለመቅረፍ የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልሉ መንግስት አካላት ጋር በመቀናጀት የጎርፍ መከላከል ስራዎች ሲያከናውን ቢቆይም የዘንድሮው ክረምት ጠንከር ያለ በመሆኑ በ6 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ ማጋጠሙን ኢዜአ ዘግቧል።

ጎርፉን ተከትሎ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም 32 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ግምቱ በመጣራት ላይ የሚገኝ ሰብልና እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ።

እስከ አሁን ድረስ በአይሳኢታ ወረዳ በጎርጉም ሁለት ቀበሌዎች ለሚገኙ ለ1 ሺህ 100 በላይ ሰዎች የፌዴራል መንግስት በሄሊኮፕተር ምግብ የማቅረብ ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል ።

ከተፈናቃዮች መካከል 17 ሺህ 450 ሰዎች በአይሳኢታ ወረዳ የ5 ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው ።

በተለይም ካለፈው እሁድ ጀምሮ በወረዳው ኮሎዱራና ገለአሊ ቀበሌዎች የአዋሽ ወንዝ ሰብሮ ወደ ቀበሌዎቹ በመግባጋቱ 1 ሺህ 126 ሰዎች በውሃ ተከበው ይገኛሉም ነው የተባለው።

ለጊዜው ክልሉ የምግብና ምግብ-ነክ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በማድረግ የህይወት አድን እርዳታ ለማቅረብ እየሞከረ ቢሆንም ከችግሩ ስፋትና አሳሳቢነት አንፃር የፌዴራል መንግስት እገዛ መጠየቁን አቶ አይዳሂስ ተናግረዋል ።

በመሆኑም ከሰላም ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት ጋር በመተባባር ከዛሬ ጀምሮ በሄሊኮፕተር አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል ።

በውሃ የተከበቡት ሰዎች በሔሊኮፕተርና በሞተር ጀልባ በማውጣት ወደ ሌላ አካባቢዎች ለማስፈር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ከዳይሬክተሩ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

በአፋር ክልል በታችኛውና መካከለኛው አዋሽ 63 ሺህ ሰዎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሲሆኑ 44 ሺህ ሰዎች በመፈናቀል ስጋት ላይ የሚገኙ ናቸው ተብሏል ።

Exit mobile version