Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

177ሺ ለሚሆኑ መዝገቦች ውሳኔ መስጠቱን የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከቀረቡለት ከ201 ሺ በላይ መዝገቦች 177ሺ ለሚሆኑት ውሳኔ መስጠቱን የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ምክር ቤት 11ኛ ጉባኤ ላይ እንዳለው ባሳለፍነው በጀት አመት በፍትሃብሄርና በወንጀል ከቀረቡለት 201 ሺ 347 መዝገቦች ውስጥ 177 ሺ 214 የሚሆኑት የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያገኙ እድርጓል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ እንዳሉት አፈጻጸሙ ከእቅዱም ሆነ ከአምናው በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሆነበት ምክንያት ኮቪድ-19 የፈጠረው ተጽዕኖ ነው።
በጠቅላይ ፍርዱ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት 3 ሺህ 156 መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን አንስተዋል፡፡

ፍርድ ቤቶችም መዛግብትን የማጣራት አቅም 96 በመቶ መድረሱንና ከመዝገቦች ውስጥ 81 በመቶው የሚሆኑት በተጠናው የጊዜ ገደብ በ2 ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ያገኙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በበጀት አመቱ የመወሰን አቅም፣የመዛግብት መጨናነቅ ሁኔታ፣የማጣራት አቅም፣የዳኛ መዝገብ ጥምርታ፣በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የመወሰን አቅም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ምክንያቱ በወረርሽኝ ምክንያት ፍርድ ቤቶች በከፊል ብቻ እንዲሰሩ መደረጉ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ለ29 ሺህ 739 መዝገቦች በተዘዋዋሪና በምድብ ችሎት ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን 19 ሺህ 166 የሚሆኑ ጉዳዮች ደግሞ በእርቅ ተቋጭተዋል ተብሏል።

ከ77ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ነጻ የህግ ድጋፍና የምክር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ነው የተባለው።

ፍርድ ቤቶቹ ልዩ ትኩረት በሚሹ የሴቶችና ህጽናት ጥቃት፣በአስገድዶ መድፈር፣በህገ ወጥ ንግድና በሰዎች ዝውውር፣በሙስናና ታክስ ማጭበርበር ጉዳዮች ዙሪያ የቀረቡ 6 ሺህ 783 መዝገቦች ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version