አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊትን እና ለሌሎች ፀጥታ አካላትን ለመደገፍ የገቢዎች ሚኒስቴር አመራሮች እና ሰራተኞች የደም ልገሳ እያደረጉ ይገኛል::
ከ200 በላይ የተቋሙ ሰራተኞች በበጎ ፍቃድ ደም የለገሱት በግዳጅ ላይ ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ከጎናቸው መሆናቸውን ለማሳየት በማለም መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል::
የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው እንደተናገሩት የሀገርን ሉዓላዊነት እና ክብር በማስጠበቅ ህግ በማስከበር ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት በዚህ ወቅት ደም በመለገስ አጋርነትን በተግባር ለማሳየት የልገሳ መርሃ ግብር መከናወኑን ተናግረዋል::
ደም መለገስ የህይወት ስጦታ በመሆኑ ህይወቱን ሳይሳሳ ለሀገሩ ለመክፈል ከተሰለፈው ጀግና ሰራዊት ጎን በዚህ ተግባር አጋርነትን በማሳየት አብሮ መቆም ይገባልም ብለዋል ሚኒስትሩ::
ደም እየለገሱ የሚገኙት ሰራተኞችም መንግስት በአጥፊው የህወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልፀዋል::
መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በሚችለው ሁሉ ከፀጥታ ሀይሉ ጎን እንዲሰለፍም ጥሪ አቅርበዋል።
በመለሰ ምትኩ